ፍትሕ ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈራረማቸው ተነግሯል፡፡
ስምምነቱ ወንጀልን አስቀድሞ ከመከላከልና ወንጀል ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁ ከማስቻል አንጻር አብሮ መሥራትና ለኅብረተሰቡ የንቃተ ሕግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትን ለመስጠት ያስችላል ሲሉ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው ተናግረዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባደረጉት ንግግር፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ የማኅበረሰብ ዐቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በ11 ክፍለ ከተሞችና በ833 ቀጠናዎች ባሉ አካባቢዎች ይህ የስምምነት ሰነድ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።
ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለሚከናወነው የወንጀል መከላከል ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ማኅበረሰቡ መብትና ግዴታውን አውቆ ሥራዎችን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን የንቃተ ሕግ ግንዛቤን ከመፍጠር አንጻር ስምምነቱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ በተጨማሪ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ እና የሕግ ትምህርት ቤቶች ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተጠቅሷል።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015