ማክሰኞ ኀዳር 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግል ለማዛወር ያወጣውን ጨረታ ለአንድ ወር ማራዘሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግስት በስኳር ፋብሪካዎች ባለቤትነትና አሠራር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ በማሰብ ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ላይ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዛወር ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል።
ጨረታው እስከ ፈረንጆቹ ኀዳር 30 ቀን ድረስ ለባለሃብቶች ክፍት የነበረ ሲሆን፥ አሁን ላይ ጨረታው ለተጨማሪ አንድ ወር እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ 31 ቀን ድረስ መራዘሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚህም የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ባለሐብቶች የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግሉ ዘርፍ ለማዛወር በወጣው ጨረታ እንዲሳተፉ ጥሪውን የቀረበ ሲሆን፤ ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3 ፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ለጨረታ መቅረባቸው ተገልጿል።
ጨረታው ተወዳዳሪነትን እና የስኳር ምርታማነትን በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ያለመ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አመላክቷል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለስኳር ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት፤ ገቢን ለማሳደግ ብሎም የሸንኮራ አገዳ አምራቾችን ሕይዎት ለማሻሻል እንደሚረዳ የታመነበት ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈም ጥሬ እና ያለቀለት የሸንኮራ አገዳ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚረዳም ተገልጿል፡፡



