ረቡዕ ኀዳር 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ ትላንት ማክሰኞ ምሽት 2:08 ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ልዩ ቦታዉ ጨፌ ስላሴ እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የሶሰትና የአራት ዓመት እድሜ ያላቸዉ ኹለት ህጻናት ህይወታቸዉ አልፏል።
በአደጋው አንድ የሰባት ዓመት ታዳጊ ጉዳት ደርሶበት ህክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሚገኝ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
አደጋው የደረሰባቸው ህጻናቶቹ እናት በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ዉስጥ ሠራተኛ ሲሆኑ፤ አደጋዉ በደረሰበት ምሽት ለሥራ ወደ ፋብሪካዉ በሄዱበት አደጋው አጋጥሟል። ሦስት ልጆች እቤት እንዳሉ በር ከዉጭ ቆልፋባቸዋለች መሄዳቸውን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ በተለይ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ።
በአካባቢዉ በሰዓቱ ኤሌክትሪክ ኃይል ስላልነበረ በቤት ዉስጥ ሻማ ተለኩሶ ነበር። ይኸው ሻማ ሳይጠፋ በተዘነጋ ቤት እሳት በመያያዙ የኹለቱን ህፃናት ህይወት ሲቀጥፍ ሌላኛውን ታዳጊ በጎረቤት እርዳታ ማትረፍ ስለመቻሉ ተነግሯል።
እንደ ንጋቱ ማብራሪያ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸዉ ደህንነት በማሰብ በልጆች ላይ በር መቆለፍን እንደመፍትሄ እየወሰዱ ይገኛሉ። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት አደጋ ሲያጋጥም ልጆች ለማምለጥ ይቸገራሉ። በዚህም ጸጸቱ ከባድ በመሆኑ ሌሎች አማራጮችን ማስተዋል ያስፈልጋል ብለዋል።
የሻማ ብርሀን አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል ባለመረዳት በሕብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንደሚታይ ጠቁመዋል። በሻማ ዙሪያ ተገቢዉ ጥንቃቄ ካልተደረገበት እንዲህ ዓይነት አደጋ ሊያጋጥም የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል።



