ረቡዕ ኀዳር 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትናንትናው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳውቋል።
ብሊንከን ከጠ/ሚ (ዶ/ር) ዐቢይ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት የሰላም ስምምነቱ አተገባበር ላይ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እየተደረገ ስላለው ጥረት መምከራቸውን ተነግሯል።
በዚህም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል እንዲሁም በአጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች ያልተገደበ ሰብአዊ ርዳታ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት እውቅና መስጠታቸውም ተገልጿል።
ኹሉም የውጭ ኃይሎች መውጣትና የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታትን ጨምሮ የሰላም ስምምነቱን በፍጥነት ተግባራዊ የመደረጉን አስፈላጊነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እንዳነሱላቸውም ተነግሯል።
በውይይቱም ብሊንከን አገራቸው አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።



