አየር መንገዱ የኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ለአፍሪካ አገሮች ክፍት እንዲሆን መስማማቱን ገለጸ

0
598

ሰኞ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) አንድ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ /SAATM/በአፍሪካ ህብረት እ.ኤ.አ በ 2018 መጽደቁን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ክፍት እንዲሆን መስማማቱን ገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለዉ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ጉባዔ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰዉ እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ ማንኛዉም የአፍሪካ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ እንዲበር ፈቃድ እንዲሰጠዉ ለሚመለከታቸዉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አስታዉቋል፡፡

ምንም እንኳ የአፍሪካ አገራት የአየር ትራንስፖርት ገበያቸዉን ክፍት ለማድረግ የተስማሙ እና በፊርማ ያጸደቁ ቢሆንም ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረጉ እንዳልሆኑ መስፍን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች አፍሪካዊ ላልሆኑ አየርመንገዶች የበረራ ፍቃድ እየሰጡ ለአፍሪካ አየርመንገዶች እየከለከሉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ አየርመንገዶች ማህበር ዋና ጸሀፊ ሚስተር አብዱራህማን በርቴ ይህ ለረዥም ጊዜ የቆየ ችግር እንደሆነ ገልጸዉ፤ ማህበሩ ከአፍሪካ ሲቪል አቪየሽን ኮምሽን ጋር በመተባበር የማስተዋወቅ እና የማግባባት ሥራዎች በመስራት ላይ እንደሆነ መናገራቸውን ኢትዮ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ዘግቧል፡፡

ለሦስት ቀናት በስካይ ላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ባለዉ የአፍሪካ አየርመንገዶች ማህበር ጉባዔ ከ400 በላይ የአየር መንገዶች እና አቪዬሽን ኩባንያዎች አመራሮች በመካፈል ላይ ይገኛሉ፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here