ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በቀን በአማካይ 6 ሺሕ 364 ተገልጋዮችን ያለቀጠሮ ማስተናገዱን ገለጸ

0
762

በተቋሙ ከተያዙ 1 ሺሕ 378 ሃሰተኛ ማስረጃዎች ውስጥ 1 ሺሕ 199 ያህሉ የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያዎች ናቸው ተብሏል
ሰኞ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በቀን በአማካይ 6 ሺሕ 364 ተገልጋዮችን ያለቀጠሮ ማስተናገዱን አስታውቋል።

ተቋሙ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ዕቅድ ክንውን አፈጻጸምን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፤ ከሀምሌ 1/2014 እስከ መጋቢት 30/2015 ድረስ ታቅደው የነበሩ የሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ ተግባራት ክንውን የተሳካ እንደነበር ገልጿል።

በዚህም በተቋሙ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች 801 ሺሕ 615 ጉዳዮችን ለማስተናገድ በዕቅድ ተይዞ 666 ሺሕ 108 ጉዳዮች በማስተናገድ የእቅዱን 83% ማከናወን መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚሁ ዘጠኝ ወራት ተቋሙ በቀን በአማካይ 6 ሺሕ 364 ተገልጋዮችን ያለቀጠሮ ማስተናገድ መቻሉም ተመላክቷል።

በተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች 793 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዞ፤ 1 ቢሊየን 172 ሚሊየን 611 ሺሕ 631 ብር ከ63 ሳንቲም በመሰብሰብ የዕቅዱን 147 ነጥብ 77 በመቶ ማሳካቱን የገለጸው ተቋሙ፤ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ 543 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቋል፡፡

የተሽከርካሪ ሽያጭና የብድር ውል ስምምነቶች ከፍተኛ ቁጥር የያዙ ሲሆን፤ ይህም ከገቢው 88 ነጥብ 84 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል፤ ተቋሙ 610 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ፈሰስ ለማድረግ አቅዶ 905 ሚሊዮን ፈሰስ በማድረግ የዕቅዱን 148 በመቶ ማከናወን መቻሉንም ገልጿል፡፡

በዚሁ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 505 ሺሕ 356 የሚሆኑ አገልግሎቶች በኦን-ላይን ሲስተም የተሰጡ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ የውክልና አገልግሎት 300 ሺሕ 357 ወይም 59 ነጥብ 43 በመቶ ድርሻ ይዟል ተብሏል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሃሰተኛ ሰነድ የመገልገል ወንጀል ተጠርጥረው 87 ጉዳዮች ወደ ሕግ እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን፤ ዘጠኝ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ 1 ሺሕ 378 ሃሰተኛ ማስረጃዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በማድረግ ሊደርስ የነበረ ጉዳት ለማስቀረት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከተያዙት ሃሰተኛ ማስረጃዎች ውስጥ 1 ሺሕ 199 ያህሉ የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ ለ10 ሺሕ 161 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ግለሰቦች፣ አካል ጉዳተኞች፣ በሕክምና ሆስፒታል ዉስጥ ለተኙ ህሙማን፣ ደረጃ መዉጣትና መዉረድ ለማይችሉ ነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ እናቶች የተቋሙ ባለሙያዎች ቅድሚያ በመስጠት ያሉበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠቱንም አስታውቋል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ከሲዳማ፣ከደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ፣ከአማራና ከኦሮምያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት ፍትህ ቢሮዎችና፣ ከፌደራል ከክልልና እና ከአዲስ አበባ ፣ፖሊስ፣ እንዲሁም ከተለያዩ የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቀ ሲሆን፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመንግስትና የግል ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here