አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ስንታየሁ ታፈሰ የተባለው ተከሳሽ የ9 ዓመት እና የ11 ዓመት እድሜ ያላቸውን ኹለት ሴት ልጆቹን በተደጋጋሚ የግብረ-ስጋ ድፍረት ወንጀል የፈጸመባቸው መሆኑ በመረጋገጡ በእስራት መቀጣቱን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ተከሳሹ በ2013፣ 2014 እና 2015 በተለያየ ቀን እና ሰዓት በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ክልል ልዩ ቦታው ኮተቤ ቦኖ ውኃ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ብቻውን የሚያሳድጋቸውን የ9 እና 11 ዓመት የሆኑ ሕጻናት ልጆቹ ላይ የወሲብ ጥቃት መፈጸሙን የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ አመላክቷል፡፡
በዚህም በአንደኛው ልጁ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸመባት ሲሆን፤ 2ኛ ልጁ ላይም በተደጋጋሚ ልብሷን አውልቆ አልጋ ላይ እንድትተኛ በማድረግ እና በመነካካት የዘር ፈሳሹን አፏ ውስጥ ያፈሰሰ በመሆኑ በፈጸመው በሕፃናት ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ-ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል መከሰሱ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
እንዲሁም ተከሳሽ ጋብቻው በስጋ ዝምድና ምክንያት አግባብ ባለው ሕግ ተከልክሎ እያለ፤ በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ በተገለጸው ጊዜና ቦታ ልጆቹ ከሆኑት 1ኛ እና 2ኛ ተበዳይ ሕጻናት ላይ በ1ኛ ተበዳይ ላይ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸመ በመሆኑ በ2ኛ ተበዳይ ላይ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የመሰለ ድርጊት የፈጸመ በመሆኑ በዘመዳሞች መካከል የሚፈፀም የግብረ-ስጋ ግንኙነት ወንጀል በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ በመተላለፍ 4 ተደራራቢ ክሶች ተመስርቶበታል፡፡
ተከሳሹ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ የሴቶችና ሕፃናት ልዩ የወንጀል ችሎት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ፤ <<ድርጊቱን አልፈጸምኩም>> በማለት ክዶ ቃሉን ሰጥቷል።
በመሆኑም የዐቃቤ ህግ 7 የሰው ምስክር እና የሠነድ ማስረጃ ማለትም፤ በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሴቶችና ሕፃናት የተቀናጀ እንክብካቤ እና ፍትህ ማዕከል የተሰጠ 1ኛ ተበዳይ ላይ የቆየ የድንግልና መገርሰስ እና አስገድዶ በሚደፍራት ጊዜ ስትጮህ በፒንሳ ጭኗን ስለሚቆነጥጣት በብዛት የሚታይ ጥቋቁር ጠባሳዎች እንዳሉ፤ እንዲሁም 2ኛ ተበዳይ የድንግልና መገርስስ ባያሳይም ብልቷን በብልቱ ይነካካት እንደነበረ እና በሚነካካት ጊዜ ስትጮህ በፒንሳ ጭኗን ስለሚቆነጥጣት በብዛት የሚታይ ጥቋቁር ጠባሳዎች እንዳሉ የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ ቀርቧል።
እንዲሁም የካቲት 12 ሆስፒታል የተበዳዮችን ዕድሜ የሚገልፅ ማስረጃ የቀረበ በመሆኑ ተመርምሮ ተከሳሽ እንዲከላከል ተብሎ ብይን በመሰጠቱ ተከሳሽ 3 የሰው የመከላከያ ምስክሮቹን አቅርቦ በማሰማት የዐቃቤ ህግን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ በተከሰሰበት የህግ ድንጋጌ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
ዐቃቤ ህግ በተከሳሽ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ባወጣው የቅጣት መመሪያ መሰረት 1ኛ ክስ በደረጃ 3 በእርከን 36፣ 2ኛ.ክስ ደረጃ 3 እርከን 17፣ 3ተኛ እና 4ኛ ክስ በመካከለኛ ደረጃ በመነሻነት እንዲያዝለትና ማክበጃ የሌለው መሆኑን በመግለፅ እንዲቀጣ አሳስቧል።
ተከሳሽም በቅጣት ማቅለያነት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑ እንደማቅለያነት በመያዝ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዚያ 20/2015 በዋለው ችሎት በ 20 /ሃያ ዓመት/ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እና ከቤተ ዘመድ መብት በተለይም ከአስተዳዳሪነት እና ከሞግዚትነት መብቱ እንዲሻር ተወስኖበታል፡፡



