ሐሙስ ግንቦት 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከ6 ሺሕ በላይ በሕንጻ ንድፍ እና በግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የሕንጻ ጥገናና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የዘርፉ አካላት እንዲሁም የዘርፉ ልሂቃን በአንድ የሚገናኙበት “ቢግ 5 ኮንትራክት ኢትዮጽያ” ዓውደርዕይ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በይፉ ተከፍቷል።
ከዓውደርዕዩ ጎን ለጎን በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አማካኝነት የተዘጋጀ የሚኒስትሮች የጋራ ፎረም የተካሄደ ሲሆን፤ በፎረሙ ላይ የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሸዴ፣ የኢንዱስትሪ ሚንስትር መላኩ አለበል፣ የትምህርት ሚንስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ከ20 በላይ የሚኒስቴር መስሪያቤት ሃላፊዎች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።



በዚህ ኢንደስትሪ ተኮር የውይይት መድረክ ላይ፤ ባለሙያዎች በየጊዜው አቅማቸውን ለማሳደግ እና ከዘመኑ ውጤቶች ጋር ለመራመድ የሚያስችሉ ዕድሎች እና የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ተነስተው ውይይ የተደረገባቸው ሲሆን፤ በዚህም በግንባታው ዘርፍ ውስጥ ስላሉ የንግድ አማራጮች፣ ስለሕንጻ ንድፍ እና ዲዛይን፣ ስለምህንድስና እና ቴክሎጂ ነክ ነጥቦች እንዲሁም ስለአዳዲስ የዘርፉ ግኝቶች ተነስተዋል።
ይህ የዘርፉ ትልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ የንግድ ትርዒት ነው የተባለለት መድረክ፤ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እውቅናና ድጋፍ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ዲ ኤም ጂ ኢቨንተስ እና ኢቴል ኢቬንተስ ኹነቱን በጋራ አስተባብረውታል።


ዓውደርዕዩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የግንባታው ዘርፍ ዕድሎችንና አማራጮችን በመጠቆም፣ በዘርፉ የተሰማሩ ግብዓት አቅራቢዎች በተለያዩ ግዙፍ ግንባታዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉና የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉም ምቹ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ተነግሯል።
በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ ከ24 አገራት የተውጣጡ ከ140 በላይ የኢግዚቢሽን አቅራቢዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከ3 አገራትን (ጣልያን፣ ቱርክ እና ቻይና) የተውጣጡ ባህል እና ወግ ከሚያስቃኙ ትዕይንቶችም እንደሚቀርቡበትም ተገልጿል።
ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆየው ይህ ዓውደርዕይ የአገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃትና የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እንደሚረዳ የተጠቆመ ሲሆን፤ የዘርፉን ተዋናዮች ለማገናኘትና አብሮ የመስራት ባህልን ለማጎልበት የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ተመላክቷል።
በተጨማሪም አዳዲስ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ውጤቶችን ለዕይታ የሚቀርቡበት ሲሆን፤ የታዳምያንን ትኩረት በመሳብ በኢትዮጵያን የግንባታ ኢንደስትሪ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡



