ከ35 ሺሕ በላይ ቤተሰቦች ተፈናቅለዋል
ሐሙስ ግንቦት 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ከሰሞኑ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ምክንያት ከ80 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ይህን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ውድመትና መፈናቀል ያስከተለ ሲሆን፤ አደጋው በተከሰተባቸው በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እና በአፋር ክልል የሰብዓዊ እርዳታው ፍላጎቱን እያባባሰ ነው ብሏል፡፡
በዚህም ከ35 ሺሕ በላይ ቤተሰቦች በጎርፍ አደጋው ምክንያት መፈናቀላቸው እና ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡
በሶማሌ ክልል ብቻ ከ23 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው እንዲሁም፤ ከ99 ሺሕ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት መውደሙ ነው የተገለጸው፡፡
አደጋው ባጋጠማባቸው አካባቢዎች የመንግሥታቱ ድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን ሰብዓዊ እርዳታ እያቀረብኩኝ ቢሆንም፤ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም ሲል አስታውቋል፡፡
የጎርፍ አደጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት የመቋቋም አቅማቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል የተባለ ሲሆን፣ ድርቁ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነቱንም እንዳባባሰው ነው የተገለጸው፡፡
የጎርፍ አደጋው የኮሌራ በሽታን ጨምሮ ሌሎች የጤና ችግሮችን እንዳስከተለም ተጠቁሟል፡፡



