ኮሚሽኑ የተሳታፊዎችን ልየታ በአራት ክልሎች እና በአንድ የከተማ መስተዳደር ሊጀምር ነው

0
830

አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በአራት ክልሎች እና በአንድ ከተማ አስተዳደር የምክክር ተሳተፊዎችን የመለየት ሥራ እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ  ልየታውን የሚጀምርባቸው ክልሎች በጋምቤላ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በሐረሪ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ሲሆኑ፣ የልየታ ሥራው የሚካሄደው  በወረዳዎች ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ ‹‹ተወካዮችን በወረዳዎች ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማስመረጥ ያስፈለገው በአንድ ጊዜና በቀጥታ ኹሉንም ዜጎች ማሳተፍ አዳጋች በመሆኑ ነው›› ያለ ሲሆን፤ በመሆኑም በወረዳዎች ውስጥ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሀሳባችንን ያሰሙልናል የሚሏቸውን ሰዎች እንዲወክሉ ሁኔታ በማመቻቸት ዜጎች በውክልና እንዲሳተፉ እንደሚደረግ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ኹሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች እና በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚደረገው አገራዊ ምክክር ላይ በውክልና ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በአሰራር  ስርአቶቹ ላይ ኮሚሽኑ በኹሉም የአገቱ ክፍሎች ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉንም ገልጿል።

በወረዳ የሚለዩ የሕብረተሰቡ ተወካዮች ወደ ክልል በመሄድ በክልሎች ከተወከሉ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ጋር በመሆን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በፌዴራል ደረጃም የሚወከሉ ባለድርሻ አካላት በተወካዮቻቸው አማካኝነት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ እንደሚሳተፉ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ለአገራዊ ምክክሩ አመቺነት በዋናነት በወረዳ ደረጃ ከሚለዩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ፤ እራሳቸውን የሚገልጹበት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው ሰዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የመንግሥት ሰራተኞች ፣ መምህራን ፣ የተገለሉ፣ የንግድ ማህበረሰብ እና ተፈናቃዮች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

እነዚህም የማህበረሰብ ክፍሎች በኮሚሽኑ ጠያቂነት እያንዳንዳቸው 50 ሰዎችን ከየወረዳቸው እና ከየሕብረተሰብ ክፍላቸው ወክለው እንደሚልኩ ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ሲያከናውን ሙሉ ሂደቱን ራሱ የሚመራውና የሚከታተለው የገለጸ ሲሆን፤ በተሳታፊ ልየታ ሥራ ላይ እገዛን ያደርጉልኛል ብሎ ያመነባቸውን የሚከተሉትን ተባባሪ አካላት መለየቱንም አስታውቋል፡፡

እነዚህም ተባባሪ አካላት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋሟት ጉባኤ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳ አስተዳደር ተወካዮች እና እንደ የአካባቢው ዓውድ የጎሳ መሪዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡

እነዚህ አካላት የሂደቱን አካታችነት፣ ግልጸኝነት፣ አሳታፊነት እና ተዓማኒነት በመታዘብና በማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወቱም በመግለጽ፤ ለሂደቱም መሳካት እያንዳንዱ ተባባሪ አካል በየወረዳው (ልዩ ወረዳው) የሚገኙ አባላቱን በመጠቀም ካሉት አባሎቻቸውን አንድ ሰው ለየወረዳው እንደሚወከል የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here