በሰሜን ሸዋ ዞን ከ30 በላይ ወረዳዎች እጅግ አስከፊ የሰላም ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

0
1253

አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሰላሳ በላይ ወረዳዎች እጅግ አስከፊ በሆነ የሰላም ችግር ውስጥ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደኣ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት የትውልድ አካባቢያቸው እና በፓርላማ ወደ ወከላቸው ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ በማቅናት ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ሕዝቡ አለበት ያሉትን ሰቆቃ አስመልክቶ ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት መረጃ ነው፡፡

በተፈጠረው የሰላም እጦት በተለይም በገጠራማ አካባቢ የሚገኙ የጤና ጣቢያዎች እና የጤና ኬላዎች በመዘጋታቸው ወላድ እናቶች እንዲሁም የሰው ልጅ ሕይወት በሕክምና እጦት እየጠፋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ከ98 በላይ የሚሆኑ አንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በመዘረፋቸው እንዲሁም ንብረቶቻቸው በመውደሙ፤ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የመማር ማስተማር ሂደቱ መቆሙን ገልጸው፤ ከ55 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዞኑ ባሉ በርካታ አካባቢዎች ላለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በነበረው የሰላም ችግር እና አለመረጋጋት የውሃ፣ የመብራት እንዱሁም የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንደሌሉም አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም በኦሮሚያ ክልል ባሉ በርካታ ሥፍራዎች መሰል ችግሮች ቢኖሩም የዚህን ዞን ለየት የሚያደርገው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተፈናቀሉ፣ እየተገደሉ፣ እየተዘረፉ እና እየተሰቃዩ ድምጽ የሚሆናቸው አካል መጥፋቱ እና ያሉበትን ችግር ተረድቶ እልባት የሚሰጥ አካል አለመኖሩን ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በዞኑ በሚገኙ እንደ ኩዩ፣ ደገም፤ ደራ፣ ግራር ጃርሶ፣ ያያ ጉለሌ፣ ደብረሊባኖስ፣ ዋጫሌ እና ጅዳ በመሳሰሉ ወረዳዎች ሕዝቡ ያለበት ሰቆቃ እጅግ አስከፊ ነው ያሉት ታዬ ደንደኣ፤ መንግሥት ባስቸኳይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የሕዝቡን ሰላም እንዲያስጠብቅ ጠይቀዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here