ቅዳሜ ግንቦት 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በራያ አላማጣ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች በዋናነት በጀት እንዲለቀቅላቸው የሚጠይቅና በፊርማ የተደገፈ አቤቱታ በቀጥታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያስገቡ መሆኑ ተገልጿል።
ለዚህም ከኹለት ሳምንት በፊት ተደርጓል የተባለው ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ በዋግኽምራ ዞን ሥር ባሉ ኮረም፣ ዛታ፣ ወፍላ ወረዳዎች እንዲሁም፤ በሰሜን ወሎ ዞን ሥር በሚገኙ አላማጣ፣ ራያ አላማጣ እና ራያ ባላ ወረዳዎች መከናወኑን የኮረም ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገብረእግዚአብሔር ደረጀ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም የወሰንና የማንነት ጥያቄ ከአራት ዓመት በፊት ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ መግባቱን ጠቅሰው፤ “አሁን የሚላከው አቤቱታ ዋና ዓላማው የአካባቢው በጀት ወደ ትግራይ ሳይሆን ወደ አማራ ክልል እንዲገባ ለመጠየቅ ነው።” ብለዋል።
“ከሕዝቡ የተሰበሰበው በፊርማ የታገዘ አቤቱታ ተደራጅቶ ወደ ምክር ቤቱ መላክ ነው የቀረው” ያሉት ኃላፊው፤ “በኮረም ከተማ የተደረገው ጥናት 74 በመቶ የሚሆኑት ወደ አማራ ክልል መካለል የሚፈልጉ መሆናቸውን አመላክቷል።” ሲሉ ተናግረዋል።
11 በመቶ የሚሆኑት መሀል ላይ የሚወላውሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንካለል ያሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አላማጣ ላይ ደግሞ 90 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች በአማራ ክልል ሥር መጠቃለልን የሚፈልጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል። ኃላፊው አቤቱታው በቅርቡ ለምክር ቤቱ እንደሚገባም አመላክተዋል።
“2010 ገደማ ያስገባነውን የማንነት ጥያቄ ምክር ቤቱ እያየው እንደሆነ እናምናለን፣ በአሁኑ አቤቱታ የምንጠይቀው በጀቱ ወደ አማራ ክልል ገብቶ ወደ ወረዳዎች እንዲተላለፍ፤ የባንክ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት የአሰራር ሥርዓቱም ወደ አማራ ክልል እንዲዞር ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኃላፊው በጀት ባለመለቀቁ ለመንግሥት ሠራተኞች በቂ ደሞዝ እየተከፈለ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የፌዴራል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሰራር ወደ አማራ ክልል ባለመዞሩ ምክንያት፣ ለአብነት የመብራት ቆጣሪ እንደማያነብ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ “መንግሥት ጥያቄያችን በአስቸኳይ ሊፈታልን ይገባል” የሚል ሰልፍ አድርገው እንደነበር የገለጹ ገብረእግዚአብሔር፤ የማንነት ጥያቄያቸው ስላልተመለሰ በበጀት ላይ የሚያቀርቡት ጥያቄም መልስ እንዳላገኘ ጠቁመዋል፡፡
“የሕወሓት መሪዎች “አካባቢው የትግራይ ክልል አካል ነው።” በማለት በጀት እየጠየቁ ይገኛል፣ እኛም እየጠየቅን ነው። ይህ የሚፈታው ግን ለመንግሥት ያቀረብነው የማንነት ጥያቄ መልስ ሲሰጠው ነው።” ሲሉ ጠቁመዋል።
ነዋሪዎቹ የራያ ግዛቶች ከ1984 በፊት በዋግኽምራ እና በራያ ቆቦ አውራጃ ይተዳደሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ለረዥም ጊዜ የምናነሳው የማንነት ጥያቄ በአግባቡ ሊመለስልን ይገባል ብለዋል፡፡



