አዲስ ማለዳ ግንቦት 17/2015 ባስተላለፈችው ዕለታዊ የዜና ጥንቅር ላይ “የመክሰም አደጋ ተጋርጦበታል የተባለው ኢዜማ” የሚል ርዕስ ያለው የዜና ዘገባ ማስተላለፏ ይታወሳል። በዘገባው ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት ከድርጅቱ መልቀቃቸውን ምንጮቿን በመጥቀስ ዘግባለች።
አዲስ ማለዳ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ አንዳንድ የፓርቲው አባላት በተለየ ሁኔታ ድርጅቱን እየለቀቁ መሆኑን በቅርበት ሥትከታተል ቆይታለች፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ሰባት የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች ከፓርቲው ለመልቀቅ እንደወሰኑ ስትሰማ አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ይበልጥ የማጣራት ተጨማሪ እድል በማግኘቷ ቀደም ብላ ስትከታተለው የቆየችውን ዜና አጠናቃ አሰራጭታለች፡፡
ለዜናው ግብዓት ይሆን ዘንድ አዲስ አበባ ላይ ከሚገኙ የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 2/14፣ የካ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 12/13፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 25 እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 19፣ እንደዚሁም አማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል በአጠቃላይ ከአምስት የምርጫ ክልሎች መረጃ ሰብስባለች።
አዲስ ማለዳ የሰራችው ዘገባ ከተሰራጨ በኋላ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የቅቡ ቅሬታዎች ነበሩ፤ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአዲስ ማለዳ አሳታሚ ቻምፒዮን ኮሙኒኬሽንስ ዜናው ላይ ያሉ ችግሮችን ለማጣራት ለኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፣ ዜናው የተሰራበት አካል ቅሬታውን መደበኛ በሆነ አግባብ ባላቀረበበት ሁኔታ ጉዳዩን መፈተሽ እንደሚቸገር በመግለፁ አሳታሚው ዜናውን በራሱ መንገድ ለማጣራት ተንቀሳቅሷል፡፡
ለዜናው መነሻ የሆኑ መረጃዎችን፣ ዜናውን እና ሌሎችን ተያያዥ ጉዳዮች ካጣራ በኋላ የሚከተለው ጭብጥ ላይ ደርሷል፡፡
- አዲስ ማለዳ የሰራችው ዘገባ ኢዜማ ካሉት የምርጫ ክልል መዋቅሮች መካከል ከአምስት የምርጫ ክልል ወረዳዎች የተገኘ መረጃን መሰረት በማድረግ የተሰራ እንጂ፤ ፓርቲው በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት ከ400 በላይ የምርጫ ክልል መዋቅሮች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ አባላቶቹን አጠቃላይ መረጃ ፈትሾ ከ70 እስከ 80 በመቶ ያህሉ እንደለቀቁ አረጋግጦ የቀረበ የዜና ዘገባ እንዳልሆነ፤
- አንባቢዎች ዜናውን የተረዱት በኹሉም የኢዜማ መዋቅር ከሚገኙ አጠቃላይ የፓርቲው አባላት መካከል ከ70 – 80 በመቶ የሚሆኑት እንደለቀቁ የሚያሳይ እንደሆነ፤ ይህም አዲስ ማለዳ ለዜናው የተጠቀመችበት ርዕስ እና መግቢያ (headline & lead) አሳሳች በመሆኑ እንደሆነ ተገንዝበናል፤
- አዲስ ማለዳ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ዜናው ከመሰራጨቱ በፊት በነሱ በኩል ያለውን እውነታ በዜናው ላይ ለማካተት ያደረገችው ጥረት የህዝብ ግንኙነት ክፍሉ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ መጀመሪያ ላይ አጣርተን እንመልሳለን ካሉ በኋላ፣ እንደቃላቸው መልሰው ሊደውሉ ባለመቻላቸው . . . በኋላም አዲስ ማለዳ ደጋግማ ስትደውል ሥልክ ባለማንሳታቸው ዜናውን ሚዛናዊ ለማድረግ እንቅፋት እንደሆነባት ተገንዝቧል፡፡
በመሆኑም ክቡራን አንባቢዎች እና ተከታታዮቻችንን ይቅርታ እየጠየቅን የዜና ዘገባውን “ኢዜማ ከአምስት የምርጫ ክልሎቹ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት አባላት እንደለቀቁበት አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰማች፡፡” በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ በትህትና ትጠይቃለች፡፡ በተመሳሳይ አዲስ ማለዳ ለዜናው የተጠቀመችበት ርዕስ እና መግቢያ አሳሳች በመሆኑ ምክንያት በፓርቲው ላይ ጉዳት እንዳስከተለ ተረድተናል፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማን) ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
ዜናው ከተሰራጨ በኋላ ከቀረበው መደበኛ ያልሆነ ቅሬታ አንፃር የአዲስ ማለዳ ዝግጅት ክፍል ጉዳዩን ይበልጥ ለመረዳት እና ተከታይ ዘገባ (follow up story) ለመስራት ለፓርቲው የህዝብ ግንኙነት መምሪያ በተደጋገሚ ብትደውልም፣ በድጋሜ ስልክ ባለማንሳት፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ካነሱ በኋላ በተገቢው መንገድ ለማናገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እና መረጃ በመስጠት ሊተባበሩ ባለመፈለጋቸው አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ሚዛናዊ ዘገባ ለማቅረብ ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ስለተፈፀመው ስህተት፣ እንዲዚሁም በስህተቱ ሳቢያ ለደረሱ ጉዳቶች ይቅርታ እንጠይቃለን።
ግንቦት 25/2015 አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
ቻምፒዮን ኮምኒኬሽንስ
የአዲስ ማለዳ አሳታሚ




እውነት ለመናገር ነባሩ የኢዜማ አባል ድርጅቱና መሪው በያዙት ከገዳዩ ብልፅግና ጋር ተጣብቆ የመቀጠል መድረሻው የማይታወቅ የቁልቁለት ጉዞ ብቻ ሳይሆን ፕሮፌሰሩ በተደጋጋሚ በሰጣቸው ለብልፅግና የወገኑ ቃለመጠየቆች ፓርቲው በህዝብ በመጠላቱ ቀደም ብሎ ቀድመው መልቀቂያም ሳያስገቡ አብዛኛው ትተው መውጣታቸው ይታወቃል።አሁን እየለቀቁ ያሉት ፓርቲው ይስተካከላል በሚል ተስፋ በውስጥ ሲታገሉ የቆዩት ብቻ ናቸው። ከምስረታው እስካሁን አባል ከነበሩት ውስጥ የቀሩት ከ10% በታች መሆናቸውን ባለኝ የቅርብ ክትትል ማረጋገጥ ችያለሁ።