በደቡብ ክልል 1ሺሕ 131 የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸው ተገለጸ

0
639

ከ4 ሺሕ በላይ ቅጥር፣ ዝውውር እና የደረጃ እድገት በሕገ ወጥ መልኩ መፈጸሙም ተነግሯል

ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ክልል ከ17 ሺሕ በላይ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ በተደረገው የማጣራት ሥራ 1ሺሕ 131ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸውን የደቡብ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ሲሆን፤ በመድረኩም የደቡብ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዘይኔ ቢልካ በበጀት ዓመቱ ከ17 ሺሕ በላይ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ በተደረገ የማጣራት ሥራ 1ሺሕ 131 የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ 5 ሸሕ 672 የብቃት ማረጋገጫ ላይ በተደረገ ፍተሻ 767 የብቃት ማረጋገጫዎች ሀሰተኛ መሆናቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በተቋማት ከ23 ሺሕ በላይ መዝገቦች ላይ ፍተሻ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው፤ ከ4 ሺሕ በላይ ቅጥር፣ ዝውውር እና የደረጃ እድገት በሕገ ወጥ መልኩ መፈጸሙንም በመጠቆም፤ ከ2 ሺሕ በላይ አመራሮች እና ባለሙያዎችን ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ144 በላይ አመራሮችን ከኃላፊነት የማንሳት ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል

በሕገ-ወጥ ቅጥር፣ ዝውውር እና ደረጃ እድገት የተገኘ ሀብት የማስመለስ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ ለዚህም የኹሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻል፣ ተቋማትን የለውጥ ማዕከል የማድረግ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን መስራት ይጠበቃል ማለታቸውን ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here