የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የሚፈጽሙት ሰዎችን የመሰወር ድርጊት እንዲቆም ኢሰመኮ ጠየቀ

0
881

ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ፡፡

ኢሰመኮ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የደረሱትን አቤቱታዎችና ጥቆማዎች መነሻ ባደረገው ክትትል በርካታ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች መፈጸማቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ አብዛኛውቹ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታና ከመንገድ ላይ በመንግሥት የጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ሥፍራ ተወስደው የተሰወሩ መሆናቸውን ኢሰመኮ ጠቁሟል፡፡

ከተሰወሩት መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን፤ ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው ተብሏል፡፡

ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፤ ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ መረጃ እስካጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል፡፡

ከተፈጸሙ ሰዎችን የመሰወር ድርጊቶች መካከል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያዝያ 24/2015 ወዲህ ብቻ በግዳጅ ተሰውረው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከተለያየ የጊዜ መጠን መሰወር በኃላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መገኘታቸውን ኢሰመኮ አመላክቷል፡፡ እነዚህ ሰዎች በግዳጅ በተሰወሩበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የቀድሞው ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደቆዩም ተጠቁሟል፡፡

በዚሁ አስገድዶ የመሰወር ሁኔታ ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ወይም የማሰቃየት ተግባር ኮሚሽኑ ምርመራውን እያደረገ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን፤ የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀ ትክክለኛው ሁኔታ ይፋ እንደሚደርግ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በባሕር ዳር እና በደብረ ብርሃን ከተማ የአስገድዶ መሰወር ሰለባዎች የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ ኮሚሽኑ ሲከታተል ቆይቶ በኋላ፤ በግዳጅ ተሰውረው የቆዩ ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ቢያንስ ሰባት ሰዎች የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሰለባ መሆናቸው አቤቱታ ቀርቦለት ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል አንድ የቀድሞ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል አባል ታኅሣሥ 6/2015 ከቢሮ ተደውሎለት ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮ እንዲመጣ ተጠርቶ ከሄደ በኋላ የተዘጋ ሲሆን፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ የት እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ አልተቻለም ተብሏል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ጥቃት ሰለባ በሆኑ ሰዎች ላይ በቀጥታ ከሚደርሰው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪም፤ በቤተሰብ ላይ የደረሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት፣ የሥነ ልቦና ጉዳት እና ጭንቀት እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰብ በሕግ ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት የሚሸርሸር አደጋ መሆኑን ኢሰመኮ መታዘቡን አብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እጅግ ውስብስብ የሆነ የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት፣ የወንጀል መከላከልና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ማናቸውም የወንጀል መከላከልና አጥፊዎችን የመቅጣት ሥራ ሙሉ በሙሉ በሕጋዊና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ ሥርዓት ብቻ እንዲመራ ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡

የተሰወሩ ሰዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ኹሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽነሩ “አስከፊ” ያሉትን አስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች የጠየቁ ሲሆን፤ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፤ “መንግሥት የአስገድዶ መሰወር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ኹሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here