በአማራ ክልል የ8ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 26 እስከ 27/2015 ድረስ ይሰጣል

1
2845

ረቡዕ ግንቦት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል የ2015 የትምህርት ዘመን ክልላዊ የ8ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 26 እስከ 27/2015 ድረስ እንደሚሰጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ/ር) ፈተናው ከሰኔ 26 እስከ 27/2015 ድረስ እንደሚሰጥ የገለጹ ሲሆን፤ ፈተናው እንደ ከዚህ ቀደሙ ኹሉ በክልል ደረጃ የሚዘጋጅ እንደሆነና የፈተና ጥያቄዎች የሚወጡትም በአዲሱ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ምክንያት 8ኛ ክፍል የተማሩትን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተፈታኝ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥቡ 50 በመቶና ከዛ በላይ መሆኑን አውቀው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ቀሪ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸውም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የ6ኛ ክፍል ፈተና እንደከዚህ ቀደሙ ኹሉ በየትምህርት ቤቶች ተዘጋጅቶ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከሰኔ 26 እስከ 27/2015 በሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና፤ 347 ሺሕ 966 ተማሪዎች በ5 ሺሕ 752 ትምህርት ቤቶች እንደሚወስዱ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፤ የ2015 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ፈተና ሰኔ 19 እና 20/2015 እንደሚሰጥ የገለጸ ሲሆን፤ የ6ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ሰኔ 26 እና 27/2015 እንደሚሰጥ ማስታወቁ ይታወሳል።

ከተማ አቀፍ ፈተናውን 75 ሺሕ 100 የ8ኛ እንዲሁም፤ 75 ሺሕ 78 የ 6ኛ ክፍል ተማሪዎች እንደሚወስዱትም ቢሮው ገልጿል።

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here