ሐሙስ ሰኔ 1 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባቢሌ ወረዳ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በቤተሰብ ደረጃ ከ16 ሺሕ 700 በላይ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች መኖራቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ በአካል መታዘቡን ገልጾ፤ ዜጎች ለረጅም ጊዜ በመጠለያ ውስጥ መቆየታቸው ተገቢ አይደለም ብሏል።
ስለሆነም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ለችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ መስጠት እንዳለባቸው ያሳሰበው ቋሚ ኮሚቴው፤ ዜጎች በውጪ ድርጅቶች ተረጂ ሆነው መኖር ስለሌለባቸው ለቀጣይ መልሶ ለማቋቋም ሥራው የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስቧል።
የባቢሌ መጠለያ ጣቢያ አደጋ ስጋት እና መልሶ ማቋቋም ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ “የሰው ልጅ ዕድሜ ልኩን ተረጂ መሆን ስለሌለበት ተፈናቃይ ዜጎችን ወደነበሩበት መመለስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።” ብሏል።
አክሎም በመጠለያ ጣቢያው ኹለት ጤና ጣቢያ እና ሦስት ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ መኖራቸውን ገልጾ፤ ተፈናቃይ ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ጠቁሟል።
በጣቢያው ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችም ለሰባት ዓመት በጣቢው እንደቆዩ አስረድተው፤ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ እና የቤተሰብ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ካለው ሕዝብ ቁጥር አንጻር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው ለመንቀሳቀስ ራስን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲሁም በቂ የሕክምና አግልግሎት አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ከስድስተኛ ክፍል በላይ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ልጆቻቸውን ለማስተማር እንደተቸገሩም ጠቁመዋል።
መንግሥት በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችን ለማቋቋም ጥረት እንደሚያደርገው ኹሉ፤ በሶማሌ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችም ከተረጅነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።



