ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአንድ ፖሊስ አዛዥ ሕይወት ሲያልፍ በአንድ የፖሊስ አባል ላይ ጉዳት ደረሰ

0
464

ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከደቡብ ምዕራብ ክልል ከሚዛን ከተማ ወደ ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ጎደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ በመጓዝ ላይ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአንድ ፖሊስ አዛዥ ሕይወት ማለፉንና በአንድ የፖሊስ አባል ላይ ጉዳት መድረሱን የጎደሬ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ።

ጉዳቱ የደረሰው በደቡብ ምዕራብ ክልል የኪ ወረዳ ልዩ ሥሙ ባያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።

የጎደሬ ወረዳ ወንጀል መከላከል ረዳት ኢንስፔክተር ኦባንግ ኡዶንግ ጥቃቱ ሰኔ 4/2015 ከምሽቱ 1 ሰዓት 30 ደቂቃ አካባቢ ላይ መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ “ግድያው የተፈጸመው የፓሊስ አባላቱ ከደቡብ ምዕራብ ክልል ሚዛን ከተማ ስልጠናቸውን ጨርሰው ወደ ጎደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ በመመለስ ላይ እያሉ ነው።” ብለዋል።ጥቃቱንም የጦር መሳሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች እንዳደረሱት ተናግረዋል።

በጥቃቱም የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን የጎደሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ሕይወት ማለፉንና በአንድ የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ ጉዳት የደረሰበት የፖሊስ አባል በቴፒ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ ተናግረዋል።በጉዳዩ ዙሪያም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን በቀጣይ እንደሚያቀርብ ያስታወቀው ፖሊስ፤ በድርጊቱ የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ ለተጎጂ ቤተሰብ መፅናናትን ተመኝቷል።

ፖሊስ ተግባሩን በፅኑ የሚያወግዝ መሆኑን እና አጥፊዎቹም ለሕግ እንዲቀርቡ ከፍትህ አካላትና ከሚመለከታቸው ጋር በትብብር እንደሚሰራም ረዳት ኢንስፔክተር ኦባንግ ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here