ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ባሉ በርካታ የሰላም ችግሮች እና ሥር የሰደዱ የሙስና ተግባራት በቀጣይ ዓመት አገራዊ ኢኮኖሚውን በ7 ነጥብ 9 በመቶ ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ ላይ ጥያቄ አቅርቧል።
ምክር ቤቱ ጥያቄውን የገለጸው በትናንትናው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ጉባዔው በፌዴራል መንግሥት የ2016 ረቂቅ በጀት ላይ በተደረገው ውይይት ላይ ሲሆን፤ በዋናነት ሰላም ሳይረጋገጥ በየተመደበው በጀት የታለመለትን ዓላማ ሊያሳካም ሆነ የታቀደው የዕድገት ምጣኔ ሊመዘገብ ይችላል ወይ ሲል ጠይቋል።
በአማራ ክልል ከፍተኛ የጸጥታ ችግሮ መኖሩን ያነሳው ምክር ቤቱ፤ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎችም ሰፊ የጸጥታ ችግሮች ባሉበት እንዴት የምጣኔ ሀብት እድገት ሊመዘገብ ይችላል ሲል ጥያቄ አቅርቧል። በተጨማሪም ቅጥር በማይፈጸምበት ሁኔታ፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ሕገወጥ በሚል እየፈረሱ፣ ሰዎች እየታገቱ በሚሊዮን ገንዘብ እየተጠየቁ እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት በጠፋበት ሁኔታ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ አዳጋች መሆኑ ተጠቁሟል።
መንግሥት ድሃ ተኮር ኢኮኖሚ እከተላለሁ ቢልም፤ የትልልቅ ፓርኮች፣ ቅንጡ መስሪያ ቤቶችና የቤተ መንግሥት ግንባታዎች የሚያሳዩት ከሚባለው በተቃራኒ የሃብታም አገራትን አካሄድ እየተከተለ መሆኑ ነውም ተብሏል። የኢህአዴግ አስተዳደር ከሚመሰገንባቸው ተግባራት አንዱ የነበረውን በአዲስ አበባ ዝቅተኛው ማህበረሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸው ኮንቲነሮች መፍረሳቸውን በማንሳት፤ ይህ ኹሉ ባለበት እንዴት የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖራል ሲል ነው ምክር ቤቱ የጠየቀው።
ሙስናን የመከላከል እርምጃም የጠራ አይደሉም ያሉት የምክር ቤቱ አባላት፤ በተለይ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ያለደረሰኝ በሚሰበሰብ ገንዝብ ሕዝቡ መከራ እያየ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ አለመሆኑን በመጥቀስም፤ በሚታዩ ብልሹ አሰራሮች ሕግና ስርዓት የሌለ ነው የሚመስለው ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ አክለውም፤ በጀቱን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል የሰላሙ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና የሰላም ማዕከል እንደሆነች ቢነሳም አሁን ላይ ያን የሚያመላክት ሰላም በአገሪቱ የለም ተብሏል።
የሕዝብና ቤት ቆጠራ በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሏል ያሉት አባላቱ፤ ያን ታሳቢ ያደረገ ምን ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ጠይቀዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ለረዥም ጊዜ መልስ ያልተሰጣቸው በርካታ የመብራት፣ የኔትዎርክ እና የመብራት ጥያቄዎች መኖራቸው ተጠቅሷል።
የምክር ቤቱ አባላት የመስተንግዶ በጀትም በደሃ አገር በአላስፈላጊ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን በማንሳት፤ የገንዝብ ሚኒስቴር ያለ አግባብ የሚባክን በጀትን ለመቆጣጠር ምን እየሠራ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተንከባላይ የግሽበት ምጣኔው 33 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን በመጥቀስም፤ ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነና እያማረረ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ መንግሥት ምን እየሰራ ነው ሲሉም ጥያቄ አንስተዋል።
በምክር ቤቱ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የገንዝበ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ መንግሥት ሰላምን የማስከበር አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፣ ይህንም እንደሚቀጥልና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀም ስርዓት እንዲኖር ጠንካራ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
እንዲሁም “በቀጣዩ በጀት ዓመት የመንግሥት ዋናኛ ትኩረት ዋጋ ማረጋጋት ላይ መስራት ነው።” ያሉት ሚኒስትሩ፤ አክለውም “ከአሜሪካ፣ አውሮፓ ሕብረትና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያለን ግንኙነት በመሻሻሉ ባለፈው ዓመት በጀት ተይዞላቸው ያልተጀመሩና የዘገዩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ይቀጥላል።” ሲሉ ጠቁመዋል።
የሥራ ቅጥርን በተመለከተም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት እይተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአነስተኛ የሰው ኃይል ውጤታማ ሥራ መስራት ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ገልጸዋል።



