ሂጅራ ባንክ በ21 ወራት ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ

0
411

አርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

ሂጅራ ባንክ አ.ማ. በ21 ወራት ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውቋል።

ባንኩ በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ፤ የባንኩን ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 162 በመቶ የትርፍ መጠን እድገት ማስመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ273 በመቶ እድገት አለው ተብሏል።

ኹለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 5 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን የገለጹት የባንኩ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አብዱሠላም ከማል፤ የባንኩን የሀብት ምጣኔ 7.1 ቢሊየን ብር ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባንኩ ደንበኛ ተኮር መርሁን በመከተል የደንበኞቹን ብዛት በ122 በመቶ እንዲሁም የቅርንጫፎቹን ብዛት ደግሞ 80 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ባንኩ በአሁኑ ሰዓት 646 ቋሚና 500 የኮንትራት ሠራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢትዮጽያ እየሰፋ የመጣውን የሥራ አጥነት ቁጥር በማጥበብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እንዲሁም በሌላው ዓለም የሚገኙ ከ165 በላይ የሆኑ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ሰጪ ባንኮች የሚገለገሉበትን የአይማል ኮር ባንኪንግ ሲስተም ከ18 የሚበልጡ ሞጁሎች በአጭር ጊዜ ተግብሮ በሥራ ላይ በማዋል ቀዳሚ መሆን መቻሉንም አመላክተዋል።

ነሀሴ 29/2013 ሥራውን የጀመረው ሂጅራ ባንክ አ.ማ. ከብሄራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት በኢትዮጽያ ሙሉ ለሙሉ ሸሪዓውን መሰረት ያደረገ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here