በትግራይ ክልል ከ75 ሺሕ በላይ አረጋዊያን የሞት አፋፋ ላይ ናቸው ተባለ

በትግራይ ክልል የጡረታ ደመወዝ ባለመከፈሉ እንዲሁም ባለው የምግብ እጦት በረሃብና በበሽታ ከ75 ሺሕ በላይ አረጋውያን የሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን የትግራይ አረጋውያን ማህበር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የማህበሩ ሊቀመንበር አርአያ ገሰሰ ማህበሩ ጡረተኛ የሆኑና ጡረታ የማይከፈላቸው በጠቅላላው 75 ሺሕ አረጋውያንን ያቀፈ መሆኑ ጠቅሰው፤ የሚበሉትና የሚጠጡት ነገር ባለመኖሩ “እጅግ ዘግናኝ ሁኔታ ውስጥ ናቸው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከሐምሌ 19/2013 ጀምሮ በተለይ ለጡረተኛ አረጋውያን ምንም ዓይነት የጡረታ ደመወዝ አለመከፈሉን ገልጸው፤ ከባለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ግን በተቆራረጠ መልኩ አልፎ አልፎ እየተከፈለ መሆኑን አመላክተዋል።

“አረጋውያኑ በወጣትነት ዘመናቸው ለአገር ሲሰሩ የኖሩ ናቸው፡፡” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ “አሁን ላይ በእርጅና እና በሕመም ምክንያት ወጥቶ መስራት አይችሉም፣ ስለዚህም ብቸኛ መተዳደሪያቸው የጡረታ ደመወዝ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለውም፤ የጡረታ ገንዘብ አንድ ሰው በሥራ ዓለም ላይ በነበረበት ወቅት “ነገ አቅሜ ሲደክም እጠቀመዋለው” ብሎ ከወር ደመወዙ ላይ እየተቀነሰ የሚቀመጥ ነው ካሉ በኋላ፤ ነገር ግን እነዚህ አረጋውያን የራሳቸውን ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም ብለዋል።

በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ላይ ተፈጸሟል በተባለው ስርቆት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ መቋረጡን አውስተውም፤ “የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ ሲገባ፣ በረሃብ እየተቀጣ ያለው ግን ምንም የማያውቀው ማህበረሰብ ሆኗል፡፡” ብለዋል።

ስለሆነም አረጋውያኑ የአገር ባለውለታ ሆነው ሳለ በረሃብና በሕመም ምክንያት እየሞቱ ነው፤ የሚመለከተው አካል አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለኹለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት በሰላም ስምምነት ከተቋጨ ወዲህ ወደ ክልሉ የሚገባው የሰብአዊ እርዳታ መጠን ቀስ በቀስ እንዲጨምር አስችሎ የነበረ ቢሆንም፣ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑና ይባስ ብሎም የሰብአዊ ድጋፉ በመቋረጡ ለውስብስብ የጤና ችግርና ለሞት የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨምረ መምጣቱ ይጠቀሳል።

በሰሜን ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 8 ሚሊየን ገደማ ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁሟሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here