የ2015 የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከወሰዱ 150 ሺሕ 184 ተማሪዎች ውስጥ 61 ሺሕ 54 ተማሪዎች ብቻ የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠት የተጀመረውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከባለፈው ሳምንት ሰኔ 30 ጀምሮ እስከ ትላንት አርብ ሐምሌ 7/2015 ድረስ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የመውጫ ፈተናውን አፈፃጸም አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ ለስድስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መውጫ ፈተና በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ለመውጫ ፈተና ሊቀመጡ ይችላሉ ብሎ ከገመተው 240 ሺሕ ተማሪዎች ውስጥ 194 ሺሕ 239 ተማሪዎች ብቁ ሆነው ለፈተና መመዝገባቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከዚህም ውስጥ ከ48 የመንግሥት ተቋማት 84 ሺሕ 627 ተማሪዎች እንዲሁም ከ171 የግል ተቋማት 109 ሺሕ 612 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
በአጠዋላይም የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡት ውስጥ ከመንግሥት ተቋማት 77 ሺሕ 981 ተማሪዎች እንዲሁም ከግል ተቋማት 72 ሺህ 203 ተማሪዎች በድምሩ 150 ሺሕ 184 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 61 ሺሕ 54 ተማሪዎች ወይም 40 ነጥብ 65 በመቶ የማለፊያውን ነጥብ ማስመዝገባቸውን በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት ለተቋማት የተማሪዎቻቸውን ውጤት የመላክ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የ2015 የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በበይነ መረብ አማካኝነት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
የ2015 የመውጫ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤታቸውን ከእሁድ ማታ ጀምሮ ለፈተናው የተሰጣቸውን User Name በመጠቀም በዚህ ሊንክ https://result.ethernet.edu.et/ ገብተው ውጤታቸውን ማወቅ ይችላሉ ተብሏል፡፡



