የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ለቢሮ ሲጠቀምበት የነበረው ቅርስ እንደታሸገበትና ሊነጠቅ መሆኑን ገለጸ

0
601

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ላለፉት ኹለት አስርት ዓመታት ለቢሮነትና ለጋለሪነት ሲጠቀምበት የነበረውን እና ቦሌ ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውን የራስ ከበደ መንገሻ የቅርስ ቤት እንዲለቅ፤ የቤቶች ኮርፖሬሽን እያስገደደው መሆኑን ገልጿል።

ማኅበሩ ችግሩን በውይይትና በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ባለበት ጊዜ፤ ሰኞ ሐምሌ 10/2015 ከሰዓት በኋላ ቤቱን ለቆ እንዲወጣ ኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ እንደላከለት ነው የገለጸው፡፡

ማኅበሩ ላለፉት ዓመታት በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶች መጠበቅና መንከባከብ ላይ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋፅዖ መጠነ ሰፊ ሆኖ ሳለ፣ የሚገኝበትን የቅርስ ቤትም በአግባቡ እየተጠቀመበት እያለ በዚህ ፍጥነት እንዲለቅ ጫና መደረጉ አሳዝኖኛል ብሏል።

ማኅበሩ ሥራውን የሚያከናውንበት ዋና ጽሕፈት ቤቱ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን በ1890 የተገነባው የአዲስ አበባ ጥንታዊ ቅርስ የራስ ከበደ መንገሻ ቤት መሆኑን አውስቷል።

ማኅበሩ በ1997 ቅርሱን ከቀበሌ ሲረከብ ውስጡ፣ በረንዳውና ግቢው በሙሉ ተዳክሞ የነበረ ሲሆን፤ ከቀበሌው ጋር ውለታ በመፈጸም ይኖሩበት ለነበሩ በርካታ አባወራዎች ካሳ ከፍሎና ቅርስነቱ እንደተጠበቀ አድሶ እንደተረከበው ገልጿል።

በመሆኑም የማኅበሩ አባላት፣ የቅርስ ተቆርቋሪዎች እና አገር ወዳድ ዜጎች ኹሉ ከማኅበሩ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

አዲስ ማለዳ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጉዳዩን አስመልክቶ የጻፈውን ደብዳቤ የተመለከተች ሲሆን፤ በዚህም በተለምዶ ቅርስ ባለአደራ ተብሎ የሚጠራውና ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድረውን ቤት፣ ማህበሩ መብት ያለው ስለመሆኑ ለማስረዳት ያቀረበው ውል ስልጣን ባለው አካል ያልተሰጠ ነው ብሏል።

ኮርፖሬሽኙ አክሎም፤ ማህበሩ ቅርሱን መንከባከብ እንዲችል እንጂ የቤቱን ንብረት መብቶች ለማስተላለፍ የተሰጠው ኃላፊነት የለም ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር በ1985 የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ላለፉት 30 ዓመታት በአገሪቱ ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here