ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት በማቆሙ ታማሚዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ 

0
340

በአዲስ አበባ የሚገኘው ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በማቆሙ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ታማሚዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ታካሚዎቹ “ሆስፒታሉ “ማሽኖች ተበላሽተዋል” በሚል ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ልኮን የተወሰነ ቀን አገልግሎቱን ካገኘን በኋላ፤ ባለፈው ቅዳሜ ዕለት “ኬሚካል እና ዕቃ የለም” በሚል ከዚህ በኋላ በግል የጤና ተቋማት ታጠቡ እንዳትመጡ ተብለናል።” ነው ያሉት።

“ስለሆነም ህመሙ ፋታ ስለማይሰጥ አስቸኳይ መፍትሄ የማይሰጥ ከሆነ ለህልፈት መዳረጋችን ነው” ሲሉ ገልጸው፤ ቢያንስ እንኳን ጊዜያዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ቀድሞ ሊነገረን ይገባ ነበር ብለዋል።

ለአንድ እጥበት ከ3 ሺሕ 500 ብር በላይ ከፍለን ለመታከም በየቦታው ብንዞርም የግል ጤና ተቋማት እንኳን ቦታ የለንም ነው የሚሉን ሲሉም ገልጸዋል።

ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ካቀረቡ ታማሚዎች መካከል አንዲት ግለሰብ፤ “እጥበቱ ከተቋረጠ አምስተኛ ቀኑ ነው፤ ዛሬን እንዴት እንደምንውል ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው ታማሚ በበኩላቸው፤ “ማሽን ተበላሽቷልና ዕቃ አልቋል በሚል በማናውቀው ምክንያት ሕክምናችን በድንገት ተቋርጦብናል፤ ሕመሙ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ አስቸኳይ እርዳታ እንፈልጋልን።” ብለዋል።

“ከዚህ ቀደምም በሳምንት ሦስት ጊዜ ሲሰጥ የነበረው የኩላሊት እጥበት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኹለት ቀን መቀነሱ ውስጣችን ፈሳሽ እንዲቀር አድርጓል ያሉት ታማሚዎቹ፤ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም አብዛኞቹ ታማሚዎች ለመተንፈስ እስከሚችገሩ ድርስ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስከ ስምንት ዓመታት ድረስ የኩላሊት እጥበት ሲከታተሉ የቆዩ 43 ታካሚዎች መኖራቸውንና ከእነዚህ ውስጥ በቅርቡ ኹለቱ ሕይወታቸው ማለፉን በመግለጽም፤ አብዛኞቹ ከክፍለ አገር የመጡ በመሆናቸው ለመድኃኒት፣ ላብራቶሪ፣ አልጋና ምግብ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታካሚዎች የዓመት ክፍያ በመክፈሉ በጳውሎስ ሆስፒታል በነጻ የኩላሊት እጥበት ሲያገኙ እንደነበር ጠቁመው፤ “በግል ጤና ተቋማት ለመታከም አቅም የሌለን ሰዎች ነን።” ብለዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አስተዳዳሪ (ፕሮቮስት) ዶክተር ሲሳይ ሦርጉ የኩላሊት እጥበት መቋረጡን ገልጸው፤ ይህም የሆነው የግብዓት እጥረት በማጋጠሙ ነው ብለዋል።

አስፈላጊ የግብዓት ቁሳቁሶች የሚቀርቡት በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አግልግሎት መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ ተቋሙ ለኹለት ዓመት የገዛልን ግብዓት በማለቁ ለቀጣይ የሚያስፈልገንን ግብዓት ለማቅረብ በጨረታ ሂደት ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም የጨረታ ሂደቱ በታሰበው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ “ለግል አቅራቢዎች ኹለት ጊዜ ጨረታ ብናወጣም ማግኘት አልቻልንም” ብለዋል።

ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልም ተመሳሳይ የግብዓት እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል። እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ ጥገና ሳይደረግላቸው የቆዩ ማሽኖችን ለመጠገን የመለዋወጫ ዕቃዎች ጉምሩክ መደረሳቸውን አመላክተዋል።

“ግብዓቶችን ለመግዛት ጥረት እያደረግን ነው” ያሉት አስተዳዳሪው፤ “ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ የግብዓት አቅርቦት እስካልተፈጠረ ድረስ የተቋረጠው የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መቼ እንደሚጀመረ እርግጠኛ መሆኑ አይቻልም።” ሲሉ ተደምጠዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here