ዓለም ባንክ ዩጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚከለክል ሕግ ማጽደቋን ተከትሎ ለአገሪቷ የሚያደርገውን ድጋፍ ማቋረጡ ተገለጸ

0
625

ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ዓለም ባንክ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ዩጋንዳ በቅርቡ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚከለክል ጠንካራ ሕግ ማጽደቋን ተከትሎ፣ ለአገሪቷ የሚያደርገውን ድጋፍ ማቋረጡ ተገልጿል።

ባንኩ ይህን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ፤ የዩጋንዳ ባለስልጣናት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን መብት ለመጠበቅ አስተማማኝ ሕግ እስካላወጡ እና የተሟላ ጥበቃ እስካላደረጉ ድረስ ለአገሪቱ የማደርገውን ድጋፍ አቋርጫለሁ ሲል ገልጿል።

ዩጋንዳ ያጸደቀችው የተመሳሳይ ጾታ ክልክላ የተቋሙን መርህ የጣሰ ነው ያለው ባንኩ፤ ድህነትን መዋጋትና ማስወገድ የሚቻለው ማንኛውንም ሰው በምርጫው፣ በማንነቱና በጾታው የሚደርስበት መድልዎና መገለል ሲቆም ብቻ ነውም ብሏል።

ስለሆነም በዩጋንዳ መንግሥት የጸደቀው ሕግ ይህን የሚጻረር መሆኑ ጠቅሶ፤ ካምፓላ ሕጉን ደግማ እንድታጤነው የማሳመን ሙከራ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

የባንኩ ፕሮጀክቶች ከዩጋንዳ አካባቢያዊና ማህበራዊ እሴቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲተገበር ንግግር ማድረጉን ገልጾ፤ የባንኩ ዓላማ  ጾታዊ መድልዎና መገለል የሚደርስባቸው ወገኖችን መጠበቅ ነው ብሏል።

በዚህም ዩጋንዳ ያጸደቀችው ሕግ ላይ ማሻሻያ እስካላደረገች ድረስ ለባንኩ የምታቀርበው የድጋፍ ጥያቄ አይኖርም ነው የተባለው።

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ ባለፈው ግንቦት ወር በፊርማቸው ያጸደቁት የጸረ ተመሳሳይ ጾታ ሕግ እስከሞት ድረስ የሚያስቀጣ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በተለይ አሜሪካና ምዕራባውያን አገራት የጸደቀውን ሕግ በጽኑ አውግዘዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ወግ እና ባህልን ያፈነገጡ ድርጊቶችን አስመልክተው ከቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ፤ የተለያዩ ባህሎችና ወጎች ያሏት ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከማህበረሰቡ ወግና ባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች እያጋጠሙ መሆኑን የተመለከተ መረጃ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ግብረሰዶማዊነት በአገራችን ሕግ ፍጹም የተከለከና በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር በመሆኑ ፖሊስ በሚደርሰው መረጃ በመመስረት በሕግ አግባብ እርምጃ  ይወስዳል ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ መግለጹም ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here