ተባብሶ በቀጠለው የሱዳን ግጭት ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

0
763

ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው የሱዳን ግጭት፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የተጀመረው ግጭት በሽታ እና ረሃብን አባብሷል ያለው ድርጅቱ፤ ከ880 ሺሕ በላይ ሱዳናዉያን ወደ ጎረቤት አገር መሰደዳቸውንም ገልጿል።

ግጭቱ ከተጀመረበት ባለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ፤ በኩፍኝ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በትንሹ 300 ሰዎች ሞተዋልም ነው የተባለው።

20 ሚሊዮን የሚደርስ የሱዳን ሕዝብ ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል የተባለ ሲሆን፤ ከሦስት ሺሕ በላይ ሰዎችም በእርስ በርስ ግጭቱ ምክንያት መገደላቸው ነው የተገለጸው።

የመንግስታቱ ድርጅት በሪፖርቱ በሱዳን የሕክምና አገልግሎት አለመኖርና የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት ሱዳናውያንን በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል ብሏል።

በምግብና የመጠጥ ውሃ እጥረት ብዙዎች ለበሽታ መዳረጋቸውን ተከትሎ በጤና ዘርፉ በደረሰው ጉዳት በየቀኑ የሰዎች ሞት እየተመዘገበ መሆኑም ተገልጿል።

ድርጅቱ አክሎም፤ በዚህ ወቅት በአገሪቱ ያለው ከባድ ዝናብ፣ ጎርፍ፣ የምግብ እጥረት እንዲሁም ውስን የሕክምና አገልግሎት በቀጣይ ወራት እንደ ኮሌራና ወባ ያሉ በሽታዎች እንዲከሰቱ ማድረጉ አቀሬ ነው ብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሱዳን ጎረቤት አገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ማክሰኞ በቻድ ዋና ከተማ በሱዳን ግጭት ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፤ የተወሰኑ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ኮሚቴ ለግጭቱ መፍትሄ ለማስገኘት ያቀረበውን ዕቅድ አጽድቀዋል።

ዕቅዱ አስተማማኝ ተኩስ አቁምና የተለያዩ የሱዳን ኃይሎችን ያካተተ ኹሉን ዓቀፍ ንግግር ማድረግን፣ የሰብዓዊ ቀውስ ስጋቶችን መቅረፍ እና ለሱዳን በጎረቤት አገራት የዕርዳታ መጋዘኖች እንዲቋቋሙ ጭምር የሚጠይቅ ነው።

ኤርትራ በስብሰባው ያልተሳተፈች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በአምባሳደር ደረጃ ስብሰባውን ተካፍላለች።

የቻዱ የሱዳን ጎረቤት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ በካይሮ እና አዲስ አበባ የጎረቤት አገራት መሪዎች በሱዳን ቀውስ ጉዳይ ያደረጉት ጉባኤ ተከታይ ነው።

በሳዑዲ አረቢያና በአሜሪካ አሸማጋይነት ኹለቱ የሱዳን ግጭት ተፋላሚ ኃይሎች ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም፤ በአንጻሩ ጦርነቱ በአየር ጥቃት ጭምር ተባብሶ ቀጥሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here