በአማራ ክልል በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ተባለ

0
495

ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ሸዋሮቢት እና ሌሎች አካባቢዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ሰላማዊ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መታሰራቸውንና መገደላቸውን የሚያመላክቱ ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎች ደርሰውኛል ሲል፤ በክልሉ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በአማራ ክልል ያለው ግጭት በሰብዓዊ መብቶች ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ እየተከታተለ መሆኑን የገለፀው ኮሚሽኑ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመደንገጉ በፊትና በኋላ ከአዲስ አበባና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መረጃዎች እየተቀበልኩኝ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች፡፡

በዚህም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች “ከባድ የመድፍ ተኩስ ጭምር ጥቅም ላይ የዋለባቸው ከፍተኛ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ” ያለው ኢሰመኮ፤ በዚህም የሰላማዊ ሰዎች እና የንብረት ጉዳት መድረሱን አመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ መንገድ ለመዝጋት የሞከሩ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጭምር መገደላቸውን ጠቅሶ፤ እስር ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች መስበራቸውን፣ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች መዘረፋቸውን እንዲሁም በቅድመ ፍርድ ያሉ እና ታራሚዎች ማምለጣቸውን አክሏል።

የአማራ ክልል መንግሥት አመራሮች የጥቃት ዒላማ መሆናቸውንም ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ፣ ባንክ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት ያሉ መሠረታዊ አገልገሎቶች መስተጓገላቸውንም በማንሳት፤ በደብረ ብርሃን ከተማ ለኹለት ቀናት፣ አራት ብዙ ሕዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በተካሄደ ከፍተኛ ውግያ፤ በሆስፒታል፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሥራ ቦታዎች ያሉ ሰላማዊ ሰዎች በመድፍና ተኩስ ልውውጥ ተገድለዋል ነው ያለው።

እንደ ደብረብርሃን፣ ፍኖተ ሰላምና ቡሬ ባሉ ከተሞች የአየር ድበደባዎች በመፈጸማቸውም በሰላማዊ ሰዎች፣ በመኖሪያ ቤቶችና ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች ጉዳት መድረሱን ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ አክሎም፤ በባህርዳር ከተማ በርካታ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች በየጎዳናውና ከቤታቸው ውጪ ተግደለዋል፣ አንዳንድ ወጣቶችን ደግሞ ለመደብደብና ለመግደል ፍለጋ ሲደረግ እንደነበረ የሚያመላክቱ ተዓማኒ መረጃዎች ደርሰውኛል ሲልም ገልጿል።

የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቱ በአማራ ክልል ብቻ የተገደበ አይደለም ያለው ኮሚሽኑ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአማራ ተወላጆችን እያሰረ መሆኑንም አንስቷል።

የፌደራሉ መንግሥት የጅምላ እስሩን እንዲያቆም፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩት እንዲፈቱ፣ እንዲሁም ኮሚሽኑን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በየእስር ቤቶቹ ጉብኝት ለማድረግ ያልተገደበ መንገድ እንዲመቻችላቸው የጠየቀው ኢሰመኮ፤ የመንግሥት ባለስጣናትን ጨምሮ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ሰላማዊ መንገዶችን ከመጠቆም ይልቅ ግጭቱን ከሚያጋግሙ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here