ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነቸው ወልቂጤ ከቀናት በፊት የተጀመረው ማንነት ተኮር እስር እና አፈና እንዲቆም የከተማው የአገር ሽማግሌዎች እና የወጣት ተወካዮች የመንግሥት አመራሮችን መጠየቃቸውን አዲስ ማለዳ ከአገር ሽማግሌዎችና ከወጣት ተወካዮች ሰምታለች።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአገር ሽማግሌ ትናንት ነሐሴ 08/2015 ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈ ቤት በማቅናት አሁን ላይ በከተማው እየተደረገ ያለው ማንነት ተኮር የጅምላ እስር እንዲቆም መጠየቃቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በከተማዋ ረዥም ዘመን ከኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጋር ተጋብተው እና ተዋልደው እንደኖሩ በመግለጽ፤ በዚህ ሰዓት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እየተደረገ ያለው እስር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ለከንቲባው ማስረዳታቸውን አውስተዋል፡፡
ከአገር ሽማግሌዎቹ እና ከወጣቶቹ አቤቱታ የቀረበላቸው የከተማዋ ከንቲባ “ሁከት አቀናጅታችኋል” ተብለው የተወሰኑ ወጣቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እንጂ በከተማው ማንነት ተኮር የጅምላ እስር መኖሩን መረጃው እንደሌላቸው ገልጸውልናል ነው ያሉት።
“እናንተ እንዳላችሁት ብሔር ተኮር እስር እና አፈና ካለ ስልክ ደውሎ መረጃውን ከሰጠን አካል ጋር ተነጋግረን የምናሳውቃችሁ ይሆናል፡፡” በማለት ከንቲባው መናገራቸውንም አክለዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሌላኛው ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ የወጣቶች ተወካይ፤ አሁን ላይ እስሩን እያስፈጸሙ ላሉ አካላትን መረጃ በመስጠት እና ቀን በሞተር ሳይክል አብሮ በመዞር የሚታሰሩ ሰዎችን ቤት ሲጠቁሙ የሚውሉ ስድስት ወጣቶች እና አንድ የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ዘርፍ ጽህፈት ቤት አመራር መሆናቸውን ገልጸዋል።
“መረጃ የሚያቀብሉት ወጣቶች “የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች” ናቸው፡፡” ካሉ በኋላም፤ ለጸጥታ ኃይሎች በሚሰጡት የተሳሳተ እና የተዛባ መረጃ ሌሊት ላይ የእስሩ እና የአፈናው ሥራው እንደሰሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዞኑን አስተዳደር ለማናገር ሙከራ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ሆኖም ዋና አስተዳዳሪው “ስብበሳ ላይ ናቸው” መባላቸው እና በከተማዋ እየተደረገ ያለው እስር በዋናነት እየተሰራ ያለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥር ስለሆነ የዞኑ እና የከተማ አስተዳደሩ ብዙም ጣልቃ እንደማይገባበት መጠቆሙን አውስተዋል፡፡
በጅምላ ከታሰሩ ሰዎች ውስጥ በብሔር አማራ የሆኑ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።
በዚህ የተነሳም የአማራ ተወላጆች ቤታቸው እንደማያድሩም ነው የተገልጸው።
በጉዳዩ ላይ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከወጣት ተወካዮች ጋር መነጋገራቸውን የጠቆሙት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንዳለ ስጦታው፤ በከተማዋ “ሁከት አደራጅታችኋል” የተባሉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ሲሰራ እንደነበር ገልጸው፤ “ማንነት ተኮር እስር አለ” ስለተባለው ግን የደረሳቸው መረጃ አለመኖሩን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አክለውም፤ በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርቡ ለአገር ሽማግሌዎች እንደሚያሳውቁ ጠቁመዋል፡፡



