ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ለእንስሳት መኖ የሚውል የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎም በፋብሪካ የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ተገልጿል።
የኤልኔት ፋውንዴሽን የእንስሳት ደህንነት አስተባባሪ ዶክተር ይመስገን ታረቀኝ፤ ለእንስሳት መኖ ግብዓት የሚውል ጥሬ ዕቃ እጥረት በማጋጠሙ ምርቱ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተለይ ለወተት እና ለስጋ ከብቶች የሚሆን መኖ ለማዘጋጀት ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ግብር መኖሩ አምራቹ ምርቱን በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲሸጥ አድርጎታል ነው ያሉት።
በተጨማሪም መኖዎችን ለማምረት የሚያገለግሉ ማዕድናት፣ ቫይታሚንና ሌሎች ግብዓቶች በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ ከዉጪ መግባታቸው፤ ለእንስሳት መኖ የዋጋ ጭምሪ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
የእንስሳት መኖ ተጠቃሚ በኹሉም የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ሆኖ ሳለ፤ የመኖ አምራች ፋብሪካዎች በብዛት የሚገኙት አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱና አዳማ አካባቢ መሆኑ ምርቱን ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ ረጅም የግብይት ሰንሰለት እንዲኖረው በማድረግ ሌላኛው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሆኗልም ነው የተባለው።
የመኖ ማቀነባበሪያዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቢኖሩ ተጠቃሚ ምርቱን በሚፈልገው ጊዜ ማግኘት ከማስቻሉም በላይ በመሃል የሚኖረውን ሰፊ የዋጋ ልዩነት መቀነስ እንደሚቻልም ተመላክቷል።
በዶሮ መኖ ላይም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሦስት ወራት በፊት 2 ሺሕ 800 ብር ይሸጥ የነበር አንድ ኩንታል የዶሮ መኖ፣ አሁን ላይ 3 ሺሕ 800 ብር እንደሚሸጥ የመኖ አምራች ድርጅቶች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ዶሮ አርቢዎች እንቁላል ሸጠው የሚያገኙት ገቢና ለመኖ የሚያወጡት ወጭ ባለመመጣጠኑም ብዙዎች ከገበያ እየወጡ ነው ተብሏል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና የአሳ ሀብት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በተቀነባበረ የእንስሳት መኖ ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ጠቅሰው፣ አንደኛው መንስኤ ለግብዓት የሚውሉ እንደ በቆሎ፣ አኩሪ አተር እና ኑግ የመሳሰሉት ሰብሎች ዋጋ መወደድ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተጨማሪም “በአምራቾች ላይ በተደጋጋሚ የሚጣል ግብር ሌላኛው ምክንያት ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ ከዓመት በፊት እንዲቀር መደረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ተከማችተው የነበሩ የመኖ ማቀነባበሪ ፉብሪካዎች አሁን ላይ በኹሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተከፈቱና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ በማንሳት፤ ይህም በትራንስፖርት እና በመሳሰሉት የሚጨመረውን ዋጋ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ነው የገለጹት።



