አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልልን በአዲስ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚል ለማደራጀት የተጠራው 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ መርሃግብር በወልቂጤ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ለቀጣይ ኹለት ተከታታይ ቀናት ቆይታውን የሚያደርግ ሲሆን፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ እና የሕገመንግሥት ማሻሻያ ረቂቅ ሰነዶች ቀርበው በምክር ቤት አባላት ውይይት ተደርጎ የሚጸድቁ ይሆናል።
የተለያዩ ሹመቶች መስጠትና ነባሩን ክልል በአዲስ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚል ምስረታ መርሃግርም እንደሚከናወን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጋር ተያይዞ የተቋማት መቀመጫዎች ጉዳይ የሰሞኑን አነጋጋሪ ጉዳይ የነበረ ሲሆን፤ በተለይም በከምባታ ጠምባሮ ዞን በኩሉ ድልድሉ ፍትሐዊ አይደለም በሚል ተቃውሞ ተነስቶም እንደነበር ይታወሳል።



