አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ለማምረት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ ናቸው፡፡
በስምምነት ፊርማው ላይ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ባደረጉት ንግግር፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን አካላት የማምረት ሥራን በማስፋፋት ያለውን የበረራ ልምድ በመጠቀም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡” ያሉ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት በ810 ሚሊየን ብር እንደሚገነባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት ነው። አየር መንገዱ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ሥራ ሲገባ የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ምርቶቹን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ነው፡፡” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን አካላትን በማምረት ለአውሮፕላን አምራች ድርጅቶች እንዲያቀርብ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘቱ ለአየር መንገዱ ትልቅ አቅም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ፋብሪካው በ40 ሺሕ ሜትር ስኩዌር መሬት ላይ እንደሚገነባ መገለጹን ኢፕድ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በመላ አገሪቱ ገንብቶ በሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና 1 ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ አቅም ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶችን በማስገባት በስራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ ተኪ ምርት በማምረት እንዲሁም ለኢንዱስትሪያላይዜሽን ግብ መሳካት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።



