“እርቅ ይውረድ፣ የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ፣ ሰላም ይታወጅ፣ ምድሪቱንም እናሳርፋት!” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

0
418

አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) “አዲስ ዓመትን በሰላም ለመቀበል እንችል ዘንድ ከጉልበት ሳይሆን ከልብ ሽብረክ በማለት፤ እርቅ ይውረድ፣ የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ፣ ሰላም ይታወጅ ምድሪቱንም እናሳርፋት!” ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመልዕክታቸው፤ “በመርከቡ ላይ ማዕበል ቢነሣ ይህ የካፒቴኑ ጉዳይ፤ ይህ የመንገደኛው ነው አይባልም” ያሉ ሲሆን፤ በኢትዮጽያ የተነሳው ማዕበል “የሁላችንም ዕዳ ነውና መፍትሔውን በጽኑ መፈለግ ይገባናል።” ብለዋል።

የቅዱስነታቸው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

መልዕክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ቀብጸት ነፍስየ ሰላመ ወረሳዕክዋ ለሠናይትየ፡- ነፍሴን ከሰላም አራቀ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ” (ሰቆ ኤር 3፡17)፤

አባታዊ የሰላም ጥሪ

በሩቅና በቅርብ ላላችሁት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ የምሕረት ፊቱን ለምንፈልግ የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋና ሰላም እንዲበዛ እየተመኘን አባታዊ የሰላም ጥሪ መልእክታችንን እንጀምራለን!

በዘመናችን የሰላምን እና የነፃነትን ጥልቅ ትርጉም ባለመረዳት ለውጦች በነውጥ ተተክተው ከእኛ የሚጠበቀውን ሳንተገብር፣ በምኞት ከመዛል በቀር የሚጨበጥ ነገር እየራቀን፤ አገራችን ኢትዮጵያ ቋሚ ነገርን እያጣች፤ ሕዝቦቿም በሰላም መኖር ሲችሉ አንዳቸው ለአንዳቸው ወጥመድ የሚያስቀምጡ፣ ጠላት ሲያረፍድ እርስ በእርስ የሚተላለቁ ሁነዋል።

በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ዓመታት ያስቆጠረውን አስከፊ ጦርነት ለመቋጨት በተበሰረው የሰላም ስምምነት የታየውን የተስፋ ጭላንጭል ሕዝቡ በሚገባ ሳያጣጥመው በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል እያገረሸ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት ሆኖ ተመልክተነዋል።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት

በመርከቡ ላይ ማዕበል ቢነሣ ይህ የካፒቴኑ ጉዳይ፤ ይህ የመንገደኛው ነው አይባልም። በታሪክ አጋጣሚም ኢትዮጵያ በምትባል መርከብ ላይ ስለተሳፈርን ራሳችን ገዳይ፣ ራሳችን ሟች ሁነን አብረን መዋጋት እንጂ አብረን መኖር ያቃተን ሕዝብ በመሆን አገራችንን የዓለም መሳለቂያ ያደረግንበት ይህ ማዕበል የሁላችንም ዕዳ ነውና መፍትሔውን በጽኑ መፈለግ ይገባናል።

ባለፉት ዓመታት ያደቀቀን የመከራ ቅብብሎሽ የገፈቱ ቀማሽ የሆንነውን ቀርቶ ለሚሰማውም የሚያሳቅቅ ነው። በአንድ በኩል ጦርነት በሌላ በኩል ረሀብ እየተፈራረቀብን፣ የሰውነት ክብር ወድቆ ሰው ቁልቁል ሲሰቀል፣ በሕይወት ሳለም በእሳት ሲቃጠል፣ በነፍሰጡር እናቶች ላይ በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ግፍ ሲፈጸም በዚህ እና በመሳሰለው ማዕበል ውስጥ የሚኖርና ልጆቹን ለማትረፍ ያልቻለ አባት መሆን ልብን ይሰብራልና በነቢዩ የኀዘን ቅኔ በጎ ነገርን እስክንረሳ ነፍሳችን ከሰላም ርቃለች በማለት የኀዘናችንን ጽናት እንገልጻለን።

የተወደዳችሁ ወገኖቻችን!

ከአካላዊ ጦርነት እስከ ቃላት ውርወራ ብዙ ጥላሸት የመቀባባት ሰለባ ሆነው የወደቁት በሚሊዮን የሚቆጠሩ _ ልጆቻችን ትምህርት ሆነውን ልባችን ዘንበል ባለማለቱ ለወደፊት ሊመጣ የሚችለው ሲታሰብ እጅግ ያስፈራልና በዐራቱም ማዕዘን ነፍጥ አንሥታችሁ ያላችሁ በሙሉ ያነገባችሁትን ገዳይ መሣርያ አውርዳችሁ ለሰላምና ለዕርቅ ቅድሚያ በመስጠት ለአንዲት አገራችሁ ሕልውና ተገዢዎች እንድትሆነ፤ መንግሥትም ልበ ሰፊ ሁኖ ሁሉንም ለውይይት እንዲሰበስብ በጽኑ እንለምናለን።

በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያላችሁ ሽማግሌዎች ሽምግልናችሁ ለዚህ ቀን ካልሆነ ለመቼም አይሆንምና በአገሩም ሽማግሌ የለም ወይ? መባሉ በሰማይ በምድር ያስወቅሳልና ልጆቻችሁን እንድትመክሩና እንድታስታርቁ ከዛሬ ጀምሮም ለሰላም ጠበቆች ሁናችሁ እንድትቆሙ አበክረን እንጠይቃለን።

በውጭ አገር የምትኖሩም እናንተ በሰላም አገር እየኖራችሁ ዘመዶቻችሁ በእሳት ሲጠበሱ ዝም ብሎ ማየት ስለማይገባ እስከአሁን ስታደርጉት እንደቆያችሁት ሁሉ አሁንም ለሰላሙ ብርቱ ጥረት እንድታደርጉ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ማኅበረ ሰብእ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረትና እገዛ እንዲያደርጉ፣ ቤተ ክርስቲያንን የምንመራ ውሉደ ክህነትም መፍትሔ መሆን ሲገባን የችግሩ አካል ሆነዋል እየተባልን ነውና ውስጣችንን አጥርተን ለወገኖቻችን በአስታራቂነት ለመድረስ ጊዜው አሁን ስለሆነ ዛሬ እንድንነሣሣ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

ዘመነ ፓትርያርክነታችን ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ ለማየት የሚያሰቅቅ መከራ የበዛበት በመሆኑ ልባችን ቢሰበርም ከመከራችን ባሻገር የእናንተ የልጆቻንን መከራ የከፋ ሆኖ ስለሚሰማን የመከራው ዳርቻ ይናፍቀናልና 2015 ዓ.ም ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ቀናት፡- “እስመ የአክለክሙ ዘኃለፈ መዋዕል፡- ያለፈው ዘመን ይበቃል” (1ኛ ጴጥ.4፡3) የሚለውን ቃለ ሐዋርያ አብነት አድርገን አሁን ያለው ችግር ወደ ሚቀጥለው ዘመን እንዳይሻገር ገትተነው ቀጣዩን አዲስ ዓመት በሰላም ለመቀበል እንችል ዘንድ ከጉልበት ሳይሆን ከልብ ሽብረክ በማለት እርቅ ይውረድ የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ ሰላም ይታወጅ ምድሪቱንም እናሳርፋት! እናሳርፋት! እያልን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን! አባታዊ መልእክታችንን

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!! አሜን!!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ 12 ቀን 2015

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here