ከአፍሪካ ቀንድ ወደ አረብ አገራት በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ሴቶች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

0
291

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከአፍሪካ ቀንድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመግባት የሚሞክሩ ሴቶች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይ ኦ ኤም) ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

በተለይም በሰሜናዊ ሶማሊያ ቦሳሶ ከተማ በኩል አደገኛ በሆነ ጉዞ ወደ ባህረ ሰላጤው አገራት ለመግባት የሚሞክሩ ሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ መጥቷል ነው ያለው።

ምንም እንኳን በዚህ መልኩ ወደ አረብ አገራት ለመሻገር የሚሞክሩ በርካታ ወንዶች ጭምር ቢኖሩም፤ የሴት ተጓዦች ቁጥር ባለፉት ኹለት ዓመታት ከ53 ሺሕ ወደ 106 ሺሕ 700 መጨመሩን አዲስ ማለዳ ከተቋሙ ሪፖርት ተመልክታለች።

ለስደት የወጡ ሴቶች በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እንዲሁም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የጉልበት ብዝበዛና እና በማያባራ የጥቃት ሰለባ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ጠቅሷል።

በሶማሊያ ቦሳሶና ሃርጌሳ በስደተኛ ማዕከላት ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ስደተኞች ብዙዎቹ ወደ ማዕከሉ የሚመጡት ሴቶች ለወራት ታግተው የቆዩ ናቸው ያለው ተቋሙ፤ በተጨማሪም በደርዘን የሚቆጠሩት ሴቶች ነፍሰ ጡሮችና ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማያውቁ ናቸው ብሏል።

እንዲሁም በየመን ዉስጥ 43 ሺሕ ገደማ ስደተኞች በአደገኛ ሁኔታ ዉስጥ መሆናቸውን ጥቅሶ፤ በቀጠለው ግጭት ውስጥ የመሳተፍ ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው ብሏል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ከፈረንጆች 2022 መጀመሪያ ጀምሮ ከ5 ሺሕ 700 በላይ በየመን የታሰሩ እና በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰላባ የሆኑ ስደተኞችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማደረጉንም አውስቷል።

እንዲሁም በየመን፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ 300 ሺሕ የሚጠጉ ተጋላጭ ለሆኑ ስደተኞች የሰብዓዊ እርዳታ ተጠቃሚ ማድረጉን በመጥቀስ፤ በቅርቡ 5 ሺሕ 631 ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደየአገራቸው እንዲመለሱ አግዣለሁ ነው ያለው።

ይህንን እርዳታ እና ድጋፍ ለማስቀጠልም አይ ኦ ኤም 58 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ጠይቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here