“የዶንጋ ሕዝብ በልዩ ወረዳ የመደራጃት የመብት ጥያቄው ሊከበር ይገባል” የዶንጋ ሕዝቦች ዲሞክራስያዊ ፓርቲ

0
293

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በከንባታ ጠምባሮ ዞን ሥር የሚገኘው የዶንጋ ሕዝብ፤ በልዩ ወረዳ የመደራጃት የመብት ጥያቄ ሊከበርለት ይገባል ሲል የዶንጋ ሕዝቦች ዲሞክራስያዊ ፓርቲ ጠየቀ፡፡

ፓርቲው በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ “የዶንጋ ሕዝብ ልዩ ወረዳ ለመሆን ያቀረበውን ጥያቄ የዞኑ መንግሥት አፍኖ ይዞታል” ያለ ሲሆን፤ “ይህን ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የዞኑን ጣልቃ ገብነት የክልሉ መንግሥት በቶሎ ሊያስቆም ይገባል” ብሏል፡፡

የዶንጋ ብሄረሰብ ከክላስተር አደረጃጀት አንዱ የሆነውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስራች ከሆኑ አስሩ ብሐሮች አንዱ መሆኑን ያስታወሰው ፓርቲው፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ በተደረጉት በስድስቱም ብሔራዊ ምርጫ ላይ መሳተፍ አለመቻሉንም አስረድቷል፡፡

እንዲሁም “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካሁን ተወካይ የሌለው ጭቁን ሕዝብ ነው” ሲልም ፓርቲው በመግለጫው ገልጿል፡፡

የዶንጋ ሕዝብ ለመደራጀት በሕግ የሚያስፈልገውን መስፈርት ኹሉ አሟልቶ ጥያቄውን ማቅረቡንም በመግለጽ፤ “ነገር ግን የዞኑና የክልሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጥያቄው እንዳይመለስ አፍነው በመያዝ ከፍተኛ ጭቆና እያደረሱ ነው” ሲልም ወቅሷል፡፡

በተጨማሪም በሀደሮ ከተማ አስተዳደርና በሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ ሰፍሮ በሚገኘው የዶንጋ ብሔረሰብ ላይ የሚፈጸመው የመደራጀት መብት አፈና እየተባባሰ መምጣቱን በማንሳት፤ ሕዝቡ ከፍተኛ እንግልት እና ኢ ሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመበት ነው ብሏል፡፡

ስለሆነም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዶንጋ ብሔረሰብ በልዩ ወረዳ የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቃሚ በማድረግ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከወዲሁ በመፍታት የብሔረሰቦችን የጋራ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ፓርቲው ጠይቋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here