ዳሸን ባንክ የ40 ሚሊየን ዶላር ብድር አገኘ

የተገኘው ብድር ባንኩ ለወጪ ንግድ የሚሰጠውን ብድር ይበልጥ ያጠናክርለታል ተብሏል

0
230

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት (ቢ አይ አይ) እና የኔዘርላንድ የሥራ ፈጠራና ልማት ባንክ የሆነው (ኤፍ ኤም ኦ) እያንዳንዳቸው 20 ሚሊየን ዶላር በድምሩ 40 ሚሊየን ዶላር ብድር ለዳሸን ባንክ ማቅረባቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የብድር አቅርቦቱ ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበውን የግብርና ምርት ለማሳደግ እና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ለማሻሻል እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡

ቢ አይ አይ እና ኤፍኤምኦ ለዳሸን ባንክ ያቀረቡት ገንዘብ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት፣ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 39 በመቶ ድርሻ ላለው እና ለወጪ ንግዱ 90 በመቶ አስተዋጽኦ ለሚያበረክተው የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም ታምኖበታል፡፡

የቀረበው ብድር ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እገዛ ያደርጋል የተባለም ሲሆን፤ በተለይ በእርሻ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሟላት ከውጪ ገበያ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

በዚህ ትብብር ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ ከዳሸን ባንክ ጋር በአመራር ስጋት አስተዳደር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበራዊ እና ስርዓተ- ጾታ ዘርፎች ዙሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ እና ለማስረፅ በቅርበት እንደሚሰሩም ተመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here