ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ሁዋዌ ኢትዮጵያ ለ7ኛው የሁዋዌ አይ ሲ ቲ ውድድር አሸናፊ ተማሪዎች እውቅና ለመስጠትና ሌሎች እንዲሳተፉ ለማበረታታት ያለመ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት አካሂዷል። በመድረኩም የ2023–2024 ውድድር መከፈቱም ይፋ ተደርጓል።
ሁዋዌ ኢትዮጵያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ 7ኛውን በኢትዮጵያ 4ኛውን የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፤ በማጣሪያ ፈተናው ከ1500 በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሳተፋቸው ይታወቃል።
ከእነሱ ውስጥም በቻይና በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ሦስተኛ ደረጃን የያዙ ዘጠኝ ተማሪዎች፤ እንዲሁም ለአህጉር አቀፍ ውድድር አሸናፊዎች በዛሬው ዕለት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ፤ የሁዋዌ አይ ሲ ቲ ውድድር ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ግንዛቤን የሚያገኙበትና ልምድ የሚቀስሙበት የዓለም አቀፍ ተሞክሮ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ ”ውድድሩ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የአይ ሲ ቲ እውቀታቸውን እና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እና ጠቃሚ ልምድ እና የተወዳዳሪነት ባህል እንዲኖራቸው ለማድረግ ያግዛል።” ያሉ ሲሆን፤ የትምህርት ሚኒስቴርም ለዘርፉ መሻሻል ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሊሚንግ የ በበኩላቸው፤ ውድድሩ የተለያዩ የአይ ሲ ቲ ርዕሰ ጉዳዮችን ስለሚሸፍን ተሳታፊዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና ፅንሰ ሀሳቦችን የመማር እድል እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎቹ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች የተግባር ልምድ እንደሚያገኙ በመግለጽ፤ ይህም ተግባራዊ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንደሚደራቸው ጠቁመዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የአይ ሲ ቲ ውድድር ለተማሪዎች ችግር ፈቺ፣ የቡድን ሥራ ተሳታፊነት፣ ሀሳባቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዴት መግለፅ እንደሚችሉ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ አስፈላጊ ክህሎት እንደሚጨምርላቸውም ተናግረዋል።
የዕውቅና ሰርተፍኬትና ሽልማት የተበረከተላቸው ተማሪዎችም በውድድሩ በመሳተፋቸው የተለያዩ ልምዶችን ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ የቴክኖሎጂ ማዕከል የሆነውንና በቻይና የሚገኘውን የሁዋዌ ዋና መስሪያቤት መጎብኘታቸው የተለየ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ውድድሩ ከተለያዩ ዓለማት ተማሪዎች ጋር የመወዳድር እድል እንደሰጣቸውም አብራርተዋል፡፡
የሁዋዌ አይ ሲ ቲ ውድድር 2022–2023 ህዳር 02/2015 ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መጀመሩ ይታወሳል።



