በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተጠቆመ

0
227

ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በምስራቅ አፍሪካ አገራት ከመጭው ዓመት ከጥቅምት እስከ ታህሳስብ ባሉት ሦስት ወራት ከፍተኛ የንብረት ጉዳት የሚያደርስ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የምስራቅ አፍሪካ በይነመንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንቢያ እና ትግበራ ማዕከል ጠቁሟል።

በዚህም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከመጠን ባለፈ ከባድ ዝናብ አማካኝነት ሊከሰት ከሚችለው የጎርፍ አደጋ ራሳቸውን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ማዕከሉ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በምስራቅ ኬንያ እንዲሁም በደቡባዊ ሶማሊያ በመጭው ዓመት ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት ከ80 በመቶ በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ገልጾ፤ በቀጠናው አገራት ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ክስተቱ ከዚህ ቀደም የተደጋጋሚ ድርቅ እና ሌሎች ተያያዥ ቀውሶች መንስኤ ከሆነው የኢሊኖ አየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር እንደሚችልም መጠቆሙን አዲስ ማለዳ ማዕከሉ ባወጣው መረጃ ላይ ተመልክታለች።

የአፍሪካ ቀንድ በአምስት ተከታታይ የዝናብ ወራት ድርቅ ያጋጠመው በመሆኑ ለዝናብ ጥገኛ ገበሬዎች ጥሩ ሊሆን ቢችልም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚጥለው ከባድ ዝናብ ውድመትን የሚያስከትል ሊሆን ይችላል ነው የተባለው።

የጎርፍ አደጋው ከሚያስከትለው የንብረት ውድመት በተጨማሪ እንደ ወባ እና ኮሌራ ላሉ ውሃ ወለድ በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችልም ተጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈም ለበረሃ አንበጣ መራባት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የከፋ ጉዳት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ የሰፋ ነው ተብሏል።

የኢሊኖ የአየር ንብረት ለውጥ ምስራቅ አፍሪካ ባላፉት አርባ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ እንዲጠቃ ምክንያት መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ድርቅ፣ ግጭት፣ የኮሮና ቫይረስ ተጽዕኖ፣ የሩስያ ዩክሬን ጦርነት እና ሌሎች ችግሮች ተደራርበው 60 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለረሃብ መዳረጋቸው ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here