በኃይል እርምጃ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት አይቻልም ሲሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

0
134

ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም እናት ፓርቲ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ አገሪቷን እየመራ ያለው መንግሥት በሚወስደው በኃይል እርምጃ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል።

“ብልጽግና መራሹ መንግሥት የግብር ሳይሆን የሥም ቅያሬ ብቻ አድርጎ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ፤ የሕዝብን ብሶት ከማድመጥ እና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ይልቅ “በእኔ ብቻ አውቅላችኋለሁ” የእውር ድንብር ጉዞ ሕዝባችንን ማጥ ውስጥ አገራችንን ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ከፋ ቀውስ እየከተታት ይገኛል፡፡” ብለዋል።

ፓርቲዎቹ አክለውም፤ እዚህም እዚያም የሚደመጡ ዋይታዎችና የድረሱልን ጥሪዎች በጆሮ ዳባ ልበስ እየታለፉ ነው ሲሉ ገልጸው፤ “መሠረታዊ የሆኑት ችግሮቻችን ሊፈቱ የሚችሉት በጥልቅ ውይይትና ንግግር ብቻ መሆኑን ደጋግመን ብንጠቅስም ያቀረብናቸውን የሰላም ጥሪዎች መንግሥት ቸል በማለት አልፏቸዋል ነው፡፡” ያሉት።

“ከሰሜኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት በውል ሳናገግም መንግሥት አሁንም በማን አለብኝነት በአማራ ክልል እያካሄደ ባለው ጦርነት ንጹሐን ዜጎች በግፍ እየተገደሉ ነው፡፡” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ “ከነሐሴ 19 እስከ 22/2015 ባሉት ቀናት ብቻ የመከላከያ ሠራዊት በደቡብ ጎንደር ዞን የእብናት ከተማ በተከታታይ በሰነዘረው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ንጹሃን ወገኖቻችን መገደላቸውን አረጋግጠናል፡፡” ብለዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ ዘመን፣ በወረታ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በላሊበላ እና በሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ላይም ጥቃቱ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ንጹሐን ዜጎች በከፍተኛ ስጋት እና መከራ ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

በተጓዳኝ ሕዝባዊ ትግሉን ተከትሎ የአገር መከላከያ ሠራዊትም እየወሰደ ባለው እርምጃ ከባድ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህም የመከላከያ ሠራዊቱ ዋነኛ ተግባር የሆነውን አገርን ከውጪ ከሚሰነዘር ጥቃት በብቃት የመከላከል ኃላፊነቱን መወጣት ወደማይችልበት ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል ብለዋል።

የአማራ ክልል ዋና ዋና መንገዶች እየተከናወነ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት በመዘጋታቸው ለዕለት ጉርስ እና ጤና አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችና የፍጆታ እቃዎች ለሕዝቡ እንዳይደርሱ ሆነዋል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በዚህ ምክንያት ጤፍን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

“በሌላ በኩል በቅርቡ በተመሠረቱት የደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች እያነሱ በሚገኙት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የክልልነት ጥያቄዎች፣ የርዕሰ ከተማ መቀመጫ ጥያቄዎች እና መንግሥት እነዚህ ጥያቄዎች እንዳይነሱ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃዎች ሌላ የቀውስ አቅጣጫ እየተከፈተ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡” በማለት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

“ስለሆነም መንግሥት በአማራ ክልል ያሰማራውን የመከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ አስወጥቶ የአገራችን ዳር ድንበር ሊጠብቅ ወደሚችልበት መደበኛ ሥራው እንዲመልስ እና ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ለአስቸኳይ አገር አድን ውይይት በሩን ክፍት በማድረግ ችግሮች በውይይትና ድርድር ብቻ ይፈቱ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“መንግሥት በክልል ምስረታ ሥም እያከናወነ የሚገኘው የክላስተር ጥርነፋ በቂ ጥናቶች ያልተደረጉበት ነው፡፡” የሚሉት ፓርቲዎቹ፣ ጉዳዩ የተነሱ መሠረታዊ የማህበረሰብ ጥያቄዎችን እና ውሳኔዎችን ያላገናዘበ በመሆኑ በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተገቢው ማስተካከያ እስኪደረግ በጊዜያዊነት ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ ሲሉም አሳስበዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here