“በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፅንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት ወደ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

0
422

አርብ ነሐሴ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፅንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት ወደ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የመከላከያ ሰራዊቱ ጥበብ በታከለበት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከስተው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን እየቀረፈ መሆኑን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “በአማራ ክልል የሕዝቡን የመብት ጥያቄ ካባ በማድረግ ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት የተንቀሳቀሰው ኃይል ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።” ሲሉ ከመከላከያ ሰራዊት ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

“የተከበረውን የፋኖ ሥም መጠቀሚያ በማድረግ የክልሉን ጸጥታ ሲያውኩ የነበሩ” ስላሏቸው ኃይሎች በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም፤ “ከጥንት ጀምሮ እንደሚታወቀው ፋኖ አገር ተወረረች ሲባል ጦርና ጋሻ ይዞ ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚሰለፍ እንጂ መልሶ የአገሩ ሰራዊት ላይ ጦር የሚመዝ አይደለም።” ያሉ ሲሆን፤ “አሁን ላይ በፋኖ ሥም እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል በዘረፋ ተግባር ላይ የተሰማራና መንገዶችን በመዝጋት የሕዝቡን ሰላም የሚያወክ ነው።” ሲሉ ገልጸዋል።

“ሕዝቡን ሰላም ሲነሳ የነበረው ኃይልም፤ የሰራው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ መልሶ እርቃኑን እንዲቀር አድርጎታል” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ይህን ኃይልም የመከላከያ ሰራዊቱ እግር በእግር እየተከታተለና እያሳደደው መሆኑን በመግለጽ፤ “አሁን ከሕዝቡ እየተነጠለ ያለውን ይህን ኃይል አቅሙን በማዳከም ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ተችሏል” ብለዋል።

ኢታማዦር ሹሙ አክለውም፤ “አገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሆነው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ ኃይሎች ለሀገርና ለህዝብ ሲል ውድ ሕይወቱን እየከፈለ ሰላም የሚያረጋግጠውን ሰራዊት ስነ-ልቦና ያልተረዱ ናቸው” ያሉ ሲሆን፤ ”ሰራዊቱ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ኹሉ ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን በአስተማማኝ እየተወጣ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን ለሰላሙ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም በመግለጽ፤ “በሀሰተኞች ሴራ ተታለው ከፅንፈኞች ጋር የተሰለፉ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሕዝቡ እንዲመለሱ” ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

መከላከያ በ2015 የበጀት ዓመት ተልዕኮውን በሚገባ መፈፀሙንም ያስታወቁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “በ2016 የበጀት ዓመትም እንደ ተቋም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው” ብለዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here