አርብ ነሐሴ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የግሪሳ ወፍ ተከስቶ 948 ሄክታር የማሽላ ሰብልን ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ በቀለ ወንድወሰን፤ መነሻውን ከኦሮሚያ ክልል ጋርዳ ወለንጭቲ ተብሎ ከሚጠራ ቦታ ያደረገ የግሪሳ ወፍ፣ በወረዳው በሚገኙ 16 ቀበሌዎች ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በ16ቱ ቀበሌዎች በተከሰተው የግሪሳ ወፍ ከአራት ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአርሶ አደሮች የማሽላ ሰብልን ሙሉ ለሙሉ በመውደሙ ድጋሚ አርሰው ሽንብራ እየዘሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
ቡድን መሪው አክለውም የግሪሳ ወፍ የተከሰተው ከ6 ሺሕ 641 ሄክታር መሬት በላይ መሆኑን ገልጸው፤ “በጥሩ ቁመና ላይ ይገኝ የነበረው ሰብል ጉዳት ቢደርስበትም የተረፈውን ለመከላከል በግብርና ሚኒስቴር በኩል እስካሁን የተደረገ እገዛ የለም፡፡” ብለዋል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ እገዛ ሊደረግ ይገባል ካሉ በኋላም፤ የግሪሳ ወፍ እያደረሰ ያለውን ውድመት በባሕላዊ መንገድ ጅራፍ በማስጮህና ቆርቆሮ ነገሮችን በመደብደብ ለመከላከል ጥረት ቢደረገም እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊገኝ አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡
የግሪሳ ወፍ በወረዳው መከሰት የጀመረው ከነሐሴ ወር መግቢያ ጀምሮ መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው፤ የወፍ መንጋው መጠን ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን ጠቁመዋል።
“ወረዳው በጤፍ እና ማሽላ ምርት የሚታወቅ ነው፡፡” ሲሉ ጠቅሰውም፤ “ከመጭው መስከረም ጀምሮ የጤፍ ሰብል የሚደርሰበት ወቅት በመሆኑ ምርቱን እንዳያወደመው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተናል፡፡” ሲሉ አክለዋል።



