ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በግብዓት እጥረት እና ሌሎች ተግዳሮቶች ምክንያት የልብ ሕክምና ማዕከሎች ተደራሽነት ላይ አሁንም ውስንነት መኖሩን የታዝማ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የልብ ሕመምና የደም ቧንቧ በሽታዎች ዋነኛ የሞት መንስዔዎች ሲሆኑ፤ ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ችግር ጀምሮ የልብ ስፔሻሊስቶች በሚፈለገው ልክ አለመኖር በዘርፉ የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የኢፌደሪ የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።
ዶ/ር ሊያ አክለውም፤ “ይሄን አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ ብዙ አካላት አሉ፡፡” ያሉ ሲሆን፤ አቅሙ ያላቸው ደግሞ ከአገር ዉጪ ሕክምናውን ለማግኘት ለብዙ ወጪ እንደሚዳረጉ አመላክተዋል።
“በየዓመቱ 30 ሺሕ የሚደርሱ ሕጻናት ከልብ በሽታ ጋር አብረው ይወለዳሉ” ያሉት ዶ/ር ሊያ፤ ከእነዚህም 9 ሺሕ ያህሉ የልብ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ከነዚህ ዉስጥ 60 በመቶዎቹ ሴት ሕጻናት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስቴር እነዚህ በሽታዎች ከመከላከል ጀምሮ ስፔሻላይዝድ የሆነ ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በፍኖተ ካርታው በግልጽ እንደተቀመጠው የልብ ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እንደ መንግሥት ተቋማት የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በታዝማ የዉስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ቦርድ ሰብሳቢና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱላዚዝ መሃመድ በበኩላቸው፤ የልብ በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ በሚያሰጋ መልኩ እየጨመረ እየመጣ መሆኑን ገልጸው፤ በበሽታው የሚጠቁት በአብዛኛው ታዳጊዎችና ወጣቶች መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል።
“ታዝማ በልብ ሕመም ለሚሰቃዩ ወገኖች መፍትሄ ለመሆን የተቋቋመ፤ በአገራችን ይሰራሉ ተብለው የማይታሰቡ የተለያዩ ከባድና እጅግ አስቸጋሪ የልብ ቀዶ ሕክምናዎችን በማድረግና በስኬት በማጠናቀቅ የማኅበረሰቡ አለኝታ የሆነ የጤና ተቋም ነው፡፡” ሲሉም ተደምጠዋል።
ከልብ ንቅለ ተከላ ዉጪ ኹሉንም አይነት የልብ ቀዶ ሕክምናዎችን በራስ አቅም ማለትም ሙሉ በ ሙሉ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ብቻ በአገር ዉስጥ መስራት የሚያስችል ሙያዊም ሆነ የመሳሪያ ቴክኖሊጂ አቅም ላይ መድረስ የቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።
ታዝማ የዉስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ለ11 ዓመታት 600 የሚደርሱ የሕጻናትና አዋቂ የልብና መሰል የቀዶ ሕክምናዎችን ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሰራ ሲሆን፤ በቀጣይ በዓመት 300 እና ከዛ በላይ ቀዶ ጥገናዎችን ለማድረግ መታቀዱ ተነግሯል።
በአለማችን ከ620 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ማለትም ከ13 ሰዎች መካከል አንዱ በልብና ልብ ነክ በሽታዎች ጋር አብሮ እንደሚኖሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች 17 ነጥብ 9 ሚሊየን ሕዝብ በነዚህ በሽታዎች እንደሚሞቱና፤ ከዚህ ዉስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ዉስጥ እንደሚገኙም ጥናቶቹ ያመላክታሉ።



