30 ኢትዮጵያውያን ህፃናት የነፃ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ሊደረግላቸው ነው

0
928

ከእስራኤል አገር በመጣ ኦልፍሰን የተሰኘ የሕክምና ተቋም ከልብ እና ከደም ዝውውር ጋር በተያያዘ በአስከፊ የጤና ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ 30 ኢትዮጵያውያን ህፃናት ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ሕክምናው በእስራኤል አገር በሚገኘው የህፃናትን ልብ ማዳንን ዓላማው ባደረገ save the child’s heart በተሰኘ የሕክምና ቡድን እና በኢትዮጵያ ህፃናት ልብ ፈንድ ጥምረት በነፃ የሚሰጥ ሲሆን በእስራኤል አገር ትምህርታቸውን በተከታተሉት ዶ/ር መኮንን እጅጉ የህክምና ቡድኑ እንደሚመራ ተገልጿል፡፡

የሕክምና አገልግሎቱ ለአንድ ሳምንት የሚሰጥ ሲሆን እስካሁንም ለመቶ ህፃናት ምርመራ በማድረግ 11 አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የደም ዝውውር ችግር ያለባቸው እንዲሁም አምስት የሕይወት አድን የልብ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ህፃናትን መለየት ተችሏል፡፡

ሕክምናው ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት የቆየበትን 25 ዓመት ምክንያት በማድረግ ለአንድ ሳምንት የሚሰጥ ነው፡፡ በሕክምናው ላይም ከእስራኤል አገር የመጡ ዶክተሮች ከኢትዮጵያውያን አጋሮቻቸው ጋር በመሆን እንደሚሳተፉ ተቋሙ አሳውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ለልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ሰባት ሺህ ህፃናት ተራ እየጠበቁ መሆኑን ማዕከሉ ማሰታወቁ የሚታወስ ሲሆን በተለያዩ ሆስፒታሎች እና በየክፍለ አገራቱ ያሉት ደግሞ ከዚህ በላይ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ የሠለጠኑ ባለሙያዎች በስፋት አለመኖር እና ሕክምናውን ለመስጠት የሚረዱ ዋና ዋና መሣሪያዎችም ማዕከሉ ውስጥ እያሉ በገንዘብ እጥረት ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ አላቂ መድኃኒቶችን ማሟላት አለመቻሉን ገልጿል፡፡

ኦልፍሰን የሕክምና ማዕከል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1995 በእስራኤል አገር የተመሰረተ እና የህፃናት የልብ ህመም እና መሰል የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ እና በማደግ ላይ ባሉ አገራት የሚኖሩ ህፃናት የተሻለ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here