እሁድ መስከረም 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሺሕ ማለፉን፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽና መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አስረሳኸኝ ጋብቼ፤ “የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቡ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሺሕ 100 በላይ ደርሷል።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ወደ ክልሉ ከገቡት ሰዎች መካከል 46 ሺሕ 375 ያህሉ ኢትዮጵያን ሲሆኑ፤ 13 ሺሕ 733 የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ አገራት ዜጎች መሆናቸውን ተናግረዋለሰ፡፡
ከሱዳን የሚፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን እና የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገቡት ጉባ እና ኩሙሩክ በተባሉ ኹለት ወረዳዎች በኩል መሆኑን ጠቅሰው፤ በኩሙሩክ ወረዳ በኩል ከ30 ሺሕ 400 በላይ እንዲሁም በጉባ ወረዳ በኩል ከ15 ሺሕ 400 በላይ ኢትዮጵያውያን መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ይህ ቁጥር የተመዘገበው ከአራት ቀናት በፊት ነው።” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት ከሱዳን የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ብቻ ከ50 ሺሕ እንደሚበልጡ ጠቁመዋል፡፡
አክለውም፤ በአሁኑ ወቅት በጦርነት ከምትታመሰዋ ሱዳን በቀን በአማካኝ ከአንድ ሺሕ እስከ ኹለት ሺሕ ሰዎች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ከሱዳን ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የገቡት የተለያዩ አገራት ዜጎች መጠለያ ጣቢያ ተዘጋጅቶላቸው መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው ቢሆንም፤ ከሱዳን የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ግን መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም ብለዋል፡፡
ከሱዳን የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን በአካባቢው በሚኖረው ማህበረሰብ ላይ ተደርበው ጊዜ እየገፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ “የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከፌደራል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ቢሆንም እየቀረበ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ለችግር ተጋልጠዋል።” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
እስካሁን ከሦስት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ ሥፍራቸውና የቀድሞ መኖሪያቸው የተላኩ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት መጠለያ ጣቢያ ሳይሰራላቸው በዘመድ ላይ ተጠልለው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የስደት ተመላሾች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በሱዳን ግጭት ሳቢያ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት በዋናነት በአማራ ክልል መተማ ድንበር በኩል ቢሆንም፤ በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ የኹለቱ አገራት ድንበር ከወትሮው የተለየ ጥበቃ እየተደረገለት በመሆኑና እና ካለው የጸጥታ ስጋት አንፃር ስደተኞች ሌላ የመግቢያ አማራጭ እንዲፈልጉ ያስገደዳቸው ይመስላል።
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በቀሰቁሱት ጦርነት 80 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በተለይም ብዙ ስደተኞች እየገቡ ባሉበት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ስጋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል።
አምስተኛ ወሩን ባስቆጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና አንድ ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።



