ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚያዝያ ወር 2015 ጀምሮ በአማራ ክልል የሚታየውን የጸጥታ ችግር በተለይ ከነሐሴ ወር 2015 ወዲህ ተስፋፍቶ ወደ ትጥቅ ግጭት ማምራቱን በመጥቀስ፤ በተለይ ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30/2015 ድረስ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንጹሃን መሞታቸውን እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ትናንት መስከረም 7/2016 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
“በተለይም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ፣ በሰሜን ጎጃም ዞን አዴትና መራዊ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደልጊ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ፣ ሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች እና በአካባቢዎቻቸው በሚገኙ አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በግጭቱ በርካታ ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው መረዳት ችያለሁ።” ነው ያለው።
በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እጅግ አሳሳቢ ናቸው ያለው ኮሚሽኑ፤ ከሐምሌ 24 እስከ ጳጉሜን 04/2015 ድረስ በተለይም በአዴት፣ ደብረማረቆስ፣ በደብረ ታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች በርካታ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን ነው የገለጸው።

የእነዚህ ግድያዎች ሰለባ ከሆኑ ሰዎች መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች እንዲሁም የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የፋኖ አባላት መሆናቸውንም ጠቁሟል።
ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችም በኮሚሽኑ እና በአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርዱ የተሟላ ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ሲልም አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ይህን መግለጫ ይፋ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ አደረኩት ባለው ክትትል፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እና የዘፈቀደ እስር እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው ብሏል፡፡
ስለሆነም በየትኛውም ወገን የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሲቪል ሰዎችን ወይም የመሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጠቡ እንዲሁም፤ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ መከላከል ጨምሮ ለሲቪል ሰዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
በማናቸውም ኹኔታ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችን በተለይም በሕይወት የመኖር መብት እና ከኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት እንዲከበሩም ጠይቋል።
በንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያ በፈጸሙና በዘፈቀደ እስራት ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ኢሰመኮ አሳስቧል።



