በጎንደር ከተማ በተከሰተው የኮሌራ በሽታ 69 ሰዎች መያዛቸው ተገለጸ

0
697

ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

በጎንደር ከተማ ሰሞኑን በተከሰተው የኮሌራ በሽታ ከ69 በላይ ሰዎች መያዛቸውን የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ በለጠ ፈንቴ፣ ከዚህ ቀደም በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በሚገኘው በርሚል ጊዮርጊስ ገዳም ውስጥ ለጸበል በሄዱ ሰዎች ላይ ድንገተኛ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፤ ከጸበሉ ቆይተው ወደ ጎንደር ከተማ በመጡ ሰዎች አማካኝነት ወረርሽኙ መዛመቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከ69 በላይ ሰዎች መያዛቸውን ጠቅሰው፤ በከተማዋ የበሽታው ምልክት መታየት የጀመረው ከባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል።

በጸበል ቦታው በተከሰተ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የአንድ እናት ሕይወት ማለፉን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የሟች ቤተሰብ አስከሬኑን ወደ ጎንደር ከተማ ይዘው በመጡበት ወቅት በሽታው መዛመቱን አስረድተዋል።

በጎንደር ከተማ በተከሰተው የኮሌራ በሽታ እስካሁን የሞተ ሰው አለመኖሩን የገለጹት የጤና መምሪያው ኃላፊ፤ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ እያገገሙ የሚወጡ ሰዎች ቢኖሩም በምትኩ ተይዘው የሚገቡ መኖራቸውን ተናግረዋል።

“በሽታው ከዚህ በላይ እንዳይስፋፋም ባለሙያዎችን በማዋቀር የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው።” ሲሉም አመላክተዋል።

በቋራ ወረዳ ከወራት በፊት በተከሰተ የኮሌራ በሽታ ከ1 ሺሕ 500 በላይ ሰዎች መያዛቸው እና የኹለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተጠቁሟል።

ይህን ተከትሎ በሽታው ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዳይስፋፋ በሚል ወደ ቋራ ወረዳ መግባትና መውጣት ተከልክሎ ቢቆይም፤ ከባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ የእንቅስቃሴ ገደቡ እንዲነሳ በመደረጉ በሽታው ጎንደር ከተማ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑ ነው የተጠቀሰው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here