በትግራይ ክልል ከጥቅምት 2 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን እንደሚታወጅ እና መርዶ እንደሚነገር ተገለጸ

0
244

ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በፌደራል መንግስሥቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ወቅት ሕይወታቸው ያለፉ ተዋጊዎችን ለመዘከር በትግራይ ክልል ከጥቅምት 2 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ክልላዊ ሀዘን እንደሚታወጅ የክልሉ የጸጥታ እና ደህንነት ኃላፊ ጀኔራል ታደሠ ወረደ አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተደር በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የጸጥታ እና ደህንነት ኃላፊ የሆኑት ጀነራል ታደሰ ወረደ በሰጡት መግለጫ፤ “3 የብሄራዊ ሀዘን ቀን ይኖሩናል” ያሉ ሲሆን፤ “ይህ ኹሉንም ትግራዋይ የሚመለከት ሀዘን ነው።” ብለዋል።

አክለውም፤ “ኹሉም ትግራዋይ በትግራይ ውስጥ ሆነ በመላው ኢትዮጵያ፤ እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኘው ለሰማዕታት ክብር የሚሰጥበት የሃዘን ቀን ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ሰማዕታቱን ለመዘከር የህሊና ጸሎት ስነስርአት እንደሚከናወን የገለጹት ጄነራሉ፤ በመጀመሪያው ቀን የሰማዕታቱ ቤተሰቦች መርዶ እንደሚነገር እና ከዚያም ቀጥሎ ያሉት ቀናት ክልላዊ የሀዘን ቀናት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መርዶ የሚነገረው እና ክልላዊ የሀዘን ቀን የሚታወጀው በጦርነቱ ሳቢያ በክልሉ ተቋርጦ የነበረው እና በተያዘው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑንም ጀነራል ታደሰ ወረደ አመላክተዋል።

ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የሃዘን ቀን የክልሉ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ፣ የመንግሥትና የግል ሚድያዎች ሰማዕታትን የተመለከቱ መልዕክቶች እንደማያስተላልፉ ተነግሯል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተደር ይህን የሀዘን ሂደት የሚያውክ ማንኛውም ነገር የተከለከለና በሕግ እንደሚጠየቅ አሳስቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here