ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) መንግሥት “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን” ለማስመታት ሲል ፋኖን እያስታጠቀ ነው ሲል ኦፌኮ ገልጿል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ጥሩነህ ገምታ ለቢቢሲ ኦሮምኛ እንደተናገሩት፤ የፌዴራሉም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በክልሉ ውስጥ ላለፉት አምስት ዓመታት እየተደረገ ላለው ቀውስ እና የንጹሃን ግድያ በተለይም በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ራሱን “ፋኖ” እያለ የሚጠራውን ኃይል በማስታጠቅ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ሥም ለማጠልሸት እና ለማስመታት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ለዚህም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከዚህ ቀደም ወደ አማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕርዳር በማቅናት፤ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ እንደደረሱ እና እንደተፈራረሙ አውስተዋል፡፡
“በኦሮሚያ ክልል የንጹሃን ሰዎችን ሞት ዕለት ዕለት መስማት የተለመደ ቢሆንም፤ በመንግሥት በኩል ምንም አይነት መግለጫ የማያወጣውም ሆነ ድርጊቱን ሲያወግዝ አካል የሌለው ለዚህ ነው።” ሲሉ አክለዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የ2016 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ “በአዲሱ ዓመት ኦሮሚያ ውስጥ ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ አይሰማም በማለት መንግሥት የየትኛውንም ኃይል ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው የሚያስተናግደው።” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይሁንና ሽመልስ ይህን ከተናገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ መስከረም 4/2016 እነዚሁ “የፋኖ” ታጣቂዎች በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ጉዞ ላይ የነበሩ 31 ሰዎችን ከመኪና አስወርደው በጅምላ እንደረሸኗቸው የአካባቢው መንግሥት አመራሮች ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኦፌኮ ይህንኑ ግድያ አስመልክቶ በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር መስከረም 19/2023 ባወጣው መግለጫ፤ ግድያውን የፈጸሙት የ “ፋኖ” ታጣቂዎች ሲሆኑ ከመንግሥት ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው በማለት ገልጿል፡፡
እነዚህ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ግድያ የሚፈጽሙ የታጠቁ ኃይሎች “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን” ሥም እናጠለሻለን በማለት፤ “በመንግሥት ፈቃድ እና ዕውቅና በክልሉ እንዳሻቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው” በማለት ኦፌኮ በመግለጫው አካቷል፡፡
በሌላ በኩል ነሐሴ ወር 2015 ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ እና ጮቢ ወረዳዎች የአገር መከላከያ ሰራዊት በርካታ ንጹሃን ዜጎችን መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች መናገራቸው ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በዛው በጮቢ ወረዳ ቆሪቻ በተባለ ቀበሌ ነሐሴ ወር 2015 ላይ መከላከያ ሰራዊት ከአንድ ቤተሰብ ስድስት ሰዎችን መግደሉን ከግድያ ሙከራው በሕይወት የተረፈ ሰው ተናግሯል፡፡
“ይሁንና ይህን ድርጊት በሚፈጽሙ የመንግሥት ኃይሎች ላይ እርምጃ ሲወሰድ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።” ያሉት ጥሩነህ፤ “ምክንያቱ ደግሞ ወንጀሉን የሚፈጽሙ አካላት ከመንግሥት ትዕዛዝ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።” ብለዋል፡፡
መንግሥትም በየጊዜው የንጹሃን ዜጎች ግድያ ሲፈጸም ዝምታን የሚመርጠው እና ድርጊቱን የማያወግዘው እጁ ስላለበት ነው።” ሲሉ አውስተዋል፡፡
በተጨማሪም መንግሥት “እንዴት አድርጌ ሥልጣን ላይ ልቆይ እችላለሁ” ከሚለው ሃሳባ እና ጭንቀት ውጪ የሰላማዊ ሰዎች ሞት ቅንጣት ታክል እንኳን እንደማያሳስበው ይህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ከቀናት በፊት ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚፈጸም ገድያ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መባባሱን በመግለጽ መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም በማለት መኮነኑ ይታወሳል፡፡



