“እንቆጳ ጉባኤ” ጥቅምት 1 እና 2 በሚሊየም አዳራሽ ይካሄዳል

0
358

ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ትኩረቱን በሥራ ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ ያደረገው “እንቆጳ ጉባኤ” የፊታችን ጥቅምት 1 እና 2/2016 በሚሊየም አዳራሽ እንደሚካሄድ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጉባኤውን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፤ “እንቆጳ” በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ንቅናቄ በማስጀምር፤ ኢትዮጵያ በተለይም በዲጂታል ረገድ ያላትን እምቅ አቅም ለአገር ውስጥና ለአለም ዓቀፍ ታዳሚዎች የማሳወቅ ንቅናቄ እየተፈጠረ መሆኑ አስታውቋል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የሥራ እና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር ድኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ ላይ ትልቅ አቅም እንዳላት ገልጸው፤ “ይህ የእንቆጳ ጉባኤም ያላትን አቅም በመጠቀም በአገሪቱ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የብሄራዊ የሥራ ጉባኤ አካል ሆኖ የእንቆጳ ጉባኤ መካሄዱ ያስታወሱት ሚንስትር ዲኤታው፤ ጉባኤዉን መካሄዱን ተከትሎ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የሚሰሩ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ በር መክፈቱን አንስተዋል፡፡

የዘንድሮው ጉባዔም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሎውሬንዶ ኤንድ አሶስዬትስ እና ከፍሎውለስ ኤቨንትስ ጋር በጥምረት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የእንቆጳ ጉባኤ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አልሚዎች፣ በፖሊሲ አውጪዎች፣ ጀማሪ ንግድ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች እንዲሁም የትምህርት ተቋማትን በአንድ መድረክ በማገናኘት በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ተመሳሳይ ራዕይ እንዲኖራቸው የማድረግ አላማ መያዙንም አብራርተዋል፡፡

በጉባኤው በክህሎት ልማት፣ በሥራ ፈጠራ ባህል ግንባታ እና ሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የፓናል ውይይቶች እንደሚደረጉ የገለጹት ሚንስትር ዲኤታው፤ ስህነምህዳሩ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለሙያዎችና መሪዎች እንዲሁም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች የሚወያዩበት፣ ስታርታፖች ድርጅታቸውን ለባለሃብቶች የሚያስተዋውቁበት ልምድ የሚለዋወጡብት እና ትስስር የሚፈጥሩበት እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡

በጉባኤው የዘርፉ ሙሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አህጉራዊ ተቋማት እና የአለማቀፍ ኮርፖሬሽኖችን ጨምሮ የ26 አገራት ተወካዮች እንደሚሳተፉበት ተነግሯል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here