ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌደሬሽን ምክር ቤት የ2016 የመጀመሪያውን የጋራ ስብሰባቸውን የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሚገኙበት ዛሬ ከቀትር በኋላ ያካሂዳሉ።
ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይም፤ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት በተገኙበት የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ የሚያቀርቡ ይሆናል።
የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኹለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ የሐይማኖት አባቶች፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙበት ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 58 (2) እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 24 (1) መሰረት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ዓመት ሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ መሆኑ መደንገጉ ይታወቃል፡፡



