ባለኃብቱ አብነት ገ/መስቀል ከመሬት ይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለማጣሪያ ምርመራ የ10 ቀን ጊዜ ለፖሊስ ተሰጠ

0
198

ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ባለኃብቱ አብነት ገብረመስቀል የ1 ሺሕ 971 ካሬ ሜትር የይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩበት ወንጀል፤ ለማጣሪያ ምርመራ የ10 ቀን ጊዜ ለፖሊስ ተሰጥቷል።

አብነት በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 2 የሚገኘውን ከሼክ አላሙዲን መሀመድ ጋር የጋራ ንብረት የሆነ የ1 ሺሕ 971 ካሬ ሜትር ይዞታ በመሸጥ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው ተጠርጥረው ነው፤ ፍርድ ቤት የቀረቡት።

በችሎቱ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ በሚመለከት የተጠርጣሪ ጠበቆች፤ “ከዚህ በፊት ምርመራ ሲደረግበት የቀረበና ዳኝነት የተሰጠበት ጉዳይን እንደ አዲስ ምርመራ ተብሎ መቅረቡ አግባብ አይደለም” በማለት የተከራከሩና ከዚህ በፊት የነበረው የምርመራ መዝገብ ይታይልን በማለት ጠይቀዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ አብነት በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ባቀረበው ምርመራ የማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ መነሻ እና የተጠርጣሪ ጠበቆች የተነሳ መከራከሪያን    መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በቀጠረው መሰረት ተሰይሟል።

ተጠርጣሪው አብነትም ከአራት ጠበቆቻቸው ጋር በችሎት ቀርበዋል።

በዚህ መሠረት ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት የተደረገው ምርመራ በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 1 ከነበረ የ3 ሺሕ 383 ካሬ ሜትር ይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ የአሁኑ የሚመሳሰል አለመሆኑንና አሁን ፖሊስ የጠየቀበት በወረዳ 2 ሥር የሚገኝ የ1 ሺሕ 971  ካሬ ሜትር የይዞታ ሽያጭ ጋር ተያይዞ መሆኑን በመጥቀስ፤ የመከራከሪያ መቃወሚያቸውን አለመቀበሉን ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የምስክር ቃል ገና ያልተቀበለ መሆኑን ተከትሎ ተጨማሪ የማጣሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ማመኑን ጠቅሶ፤ ጠበቆች የጠየቁት ዋስትና ጥያቄን ለጊዜው አለመቀበሉን  በማብራራት ለፖሊስ የ10 የምርመራ ማጣሪያ ቀን ፈቅዷል።

በዚህ ጊዜ የአብነት ጠበቆች ከዚህ በፊት በሐምሌ ወር በጉዳዩ ላይ ምርመራ መደረጉን ዐቃቤ ሔግ ገልጾ፣ ከአገር እንዳይወጡ እግድ ተጠይቆበት ዳኝነት ተሰጥቶበታል ያሉትን ሰነድ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትላቸው በመጠየቅ ሰነዱን በችሎት አቅርበዋል።

የጊዜ ቀጠሮ ዳኞቹ ለደቂቃዎች ከችሎት ወጥተው በጽ/ቤት ሰነዱን ተመልክተው ተወያይተው በመመለስ፣ “በመዝገብ ቁጥሩ በተጠቀሰበት ሰነድ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ተደርጓ የተጣራ ነገር ስለመኖሩ አያሳይም” ብለዋል።

በዚህም ችሎቱ የጠበቆቹን አቤቱታ አለመቀበሉን በመግለጽ አስቀድሞ ለፖሊስ የሰጠውን የ10 ቀን ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ያጸና ሲሆን፤ የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅም ለጥቅምት 9/2016 ቀጠሮ መሰጠቱን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።

አብነት ገ/መስቀል የቦሌ ታወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጅምር ግንባታ ያለበት 3 ሺሕ 383 ካሬ ሜትር ይዞታን ያለአግባብ ባለመብት በመሆን፣ ይዞታው ላይ ካርታ በማውጣት ከ321 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሸጥ አድርገዋል ተብለው፤ ከሌሎች ከመሬት አስተዳደር ሠራተኞች ጋር በ2ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ላይ ከአንድ ወር በፊት ዋስትና ተፈቅዶላቸው እንደነበር ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here